ዘመናዊ አሰራርን በመዘርጋት ሌብነትን ለመቀነስ እየተሰራ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መልከ ብዙና ዋነኛ ሀገራዊ ፈተና የሆነውን ሌብነት ዘመናዊ አሰራር በመዘርጋት ለመቀነስ እየተሰራ ነው አሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመር መንግሥት በተሰኘው አዲሱ መጽሐፋቸው ዙሪያ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ ሌብነት ሰዎች ስልጣናቸውን በመጠቀም በነጻ መስጠት ያለባቸውን አገልግሎት ለሃብት ማከማቻነት ሲጠቀሙበት ነው ብለዋል፡፡
ይህም አነስተኛ ዝርፊያ መሆኑን ጠቅሰው፥ የመንግስት ሰራተኞች የተሰጣቸውን አደራ ወደ ጎን በመተው ለሚሰጡት አገልግሎት ሲያስከፍሉ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ሰዎች ያላቸውን የትኛውንም ሙያ እንደመሳሪያ በመጠቀም አላስፈላጊ ጥቅም ለማግኘት ሲሞክሩ ይስተዋላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ይህም አነስተኛ ሙስና እንደሆነ ተናግረዋል።
የመደመር መንግስት ይህን አይነቱን ሌብነት በአረም መልኩ እንደሚመለከተው ጠቅሰው፥ አረምን ለይቶ ማወቁ ለመንቀል ቀላል ቢያደርገውም ብዛቱ እና ከማሳው ጋር መመሳሰሉ ስራውን አታካች ያደርገዋል ብለዋል፡፡
ይህ አይነቱ ሌብነት ብዙ እና ለልየታ አዳጋች ቢሆንም ከተለየ ለመንቀል ቀላል መሆኑን ገልጸዋል።
ሌላው የሌብነት ዓይነት ከባድ ዝርፊያ መሆኑን በመጥቀስ በግለሰቦችና ቡድኖች መካከል በቅንጅት የሚሰራ ነው ብለዋል፡፡
ይህም አንዳንዶች ስልጣን ይዘው፣ አንዳንዶች ሚዲያ ይዘውና ሌሎች ደግሞ የጦር መሳሪያ ይዘው የሚፈጽሙት የተቀናጀ ዝርፊያ መሆኑን አብራርተዋል።
መንግስታት ከባዱን ዝርፊያ ቢመለከቱ እንኳን ለመንቀል ያስቸግራቸዋል ነው ያሉት፡፡
መሰል ዝርፊያዎች እንደ ዋርካ የሚታዩ ሆኖም ግን በቀላሉ ለመንቀል የሚያዳግቱ ሲሆን በሀገር ደረጃ ካደጉ የመንግስትን ፖሊሲና አቅጣጫ የሚወስኑ እንደሆነ ገልጸዋል።
መንግስትም በአቻነት ስሜት የሚያያቸው ይሆናሉ ብለዋል፡፡
ይህም በተለያዩ ሀገራት እንደሚታይ አንስተው፥ በኢትዮጵያም ከለውጡ በፊት በግልጽ ሲታይ እንደነበር አስታውሰዋል።
ባለስልጣናት ከባለሃብቶች ጋር ተመሳጥረው ህግ ሲያወጡና ያሻቸውን ሲዘርፉ የነበሩበት ሁኔታ ነበር ነው ያሉት፡፡
ከለውጡ በኋላ በተሰራው ስራ መሰል ዝርፊያ አለመኖሩን ተናግረዋል።
የመደመር መንግስት በስፋት የሚስተዋለውን አነስተኛ ዝርፊያ ለመንቀል ስርዓት ዘርግቶ ለማስወገድ በስፋት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
በመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትን ጨምሮ ሞባይል ባንኪንግና ዘመናዊ ግብይቶች መፈጠራቸው ችግሩን ይቀርፋል ነው ያሉት፡፡
በአቤል ነዋይ