በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የመሠረተ ልማት ስራዎች የግብር ከፋዮች ውጤት ናቸው – አቶ አሻድሊ ሀሰን
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እየተከናወኑ የሚገኙ የመሠረተ ልማት ስራዎች የግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ውጤቶች ናቸው አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን፡፡
ክልላዊ የታክስ ንቅናቄ፣ የግብር ከፋዮችና ባለድርሻ አካላት የዕውቅና መድረክ በአሶሳ ከተማ ተካሂዷል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅቱ እንደተናገሩት፥ በክልሉ ግብር ከፋዮች ከመንግስት ጋር በመተባበር በሚከናወኑ የመሠረተ ልማት ስራዎች ላይ የራሳቸውን አሻራ እያሳረፉ ይገኛሉ፡፡
ግብር የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያግዝ የዜግነት ግዴታ መሆኑን ጠቅሰው፥ ግብር ከፋዩ በታማኝነት የተጣለበትን ግብር በጊዜው መክፈል እንዳለበት አሳስበዋል።
የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ተፈሪ አበበ በበኩላቸው በተያዘው በጀት ዓመት በክልሉ 8 ቢሊየን ብር ግብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ትግበራ መገባቱን ተናግረዋል።
በክልሉ በቴክኖሎጂ የታገዘ የታክስ አስተዳደር ስርዓት በመዘርጋት ውጤታማ የገቢ አሰባሰብ ስራ እየተከናወነ ይገኛልም ነው ያሉት፡፡
በመድረኩ ላይ ግብርን በታማኝነት ለከፈሉ እና በገቢ አሰባሰብ የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ተቋማት ዕውቅና መሰጠቱን ኢዜአ ዘግቧል፡፡