ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሀገራት የፋሽን ጉባዔ ላይ ተሳተፈች
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በሩሲያ ሞስኮ በተካሄደው የ2025 የብሪክስ አባል ሀገራት የፋሽን ጉባኤ ላይ ተሳትፋለች።
በመድረኩ የኢትዮጵያ የፋሽን ኢንዱስትሪ ተዋናዮች ከዓለም አቀፍ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር ተገናኝተው ዘርፉን ለማሳደግ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማጎልበት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።
ከ60 ሀገራት የተውጣጡ 1 ሺህ ተወካዮች በተገኙበት በዚህ መድረክ ባህላዊ ትርዒቶች፣ ፈጠራዎች፣ ዘላቂ እድገትና የፋሽን ዘርፉ ስራዎች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡
በዚህም ባለሃብቶችን ወደ ፋሽን ኢንዱስትሪው መሳብ እንደሚቻልና የገበያ ዕድልን ማስፋት የሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ተደርጓል።
ዘርፉን ለማሳደግ የብሪክስ አባል ሀገራት በትብብር መስራት እንዳለባቸው መነሳቱን ቲቪ ብሪክስ ዘግቧል።
በብሪክስ ፋሽን ጉባኤ የተፈጠረው ግንኙነት ኢንዱስትሪውን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማሳደግ ሚናው ከፍተኛ መሆኑም ተመላክቷል።