የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በአፍሪካውያን ዘንድ መነቃቃትን ፈጥሯል – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የይቻላል መንፈስን ከቃል ወደ ተግባር በመቀየር በአፍሪካውያን ዘንድ ዳግም መነቃቃትን ፈጥሯል አለ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፡፡
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በወቅታዊ የውጭ ግንኙነት ተግባራት ዙሪያ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፥ የግድቡ መጠናቀቅ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ስኬት የታየበት ነው ብለዋል፡፡
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቁ በአፍሪካውያን ዘንድ ዳግም መነቃቃትን የፈጠረ ታላቅ ድል መሆኑን ገልጸው፥ የምረቃው ሁነት የዓለም አቀፉን ማህበረሰብና የዓለም መገናኛ ብዙሃንን ትኩረት ስቧል ነው ያሉት፡፡
ግድቡ የይቻላል መንፈስ ከቃል ወደ ተግባር የተቀየረበት መሆኑን በማንሳት፥ ኢትዮጵያ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ የመጨረስ ውጤታማ የፕሮጀክት አመራር ልምዷን ለሌሎች የምታካፍልበት መሆኑንም ገልጸዋል።
የግድቡ መጠናቀቅ ኢትዮጵያ በአፍሪካና በቀጣናው የምትጫወተውን ዲፕሎማሲያዊ ሚና የሚያሳድግ ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤና በአፍሪካ ካሪቢያን ሀገራት ማህበረሰብ ጉባኤዎች ላይ ውጤታማ ስራዎችን ማከናወኗን ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣይ በሚካሄደው 80ኛው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በአዲስ አበባ በተደረጉ ዓለም አቀፍ ሁነቶች የተገኙ ውጤቶችን ቀምራ እንደምታቀርብና ንቁ ተሳትፎ እንደምታደርግ ጠቁመዋል።
ከጠቅላላ ጉባኤው ጎን ለጎን አጋርነትን የሚያጠናክሩ ውይይቶችን እንደምታደርግ ተናግረዋል፡፡