ሲዲሲ አፍሪካ የመድሀኒት ምርትን ለማሳደግ የ3 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ይፋ አደረገ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ በሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከል (ሲዲሲ አፍሪካ) በአህጉሪቱ የክትባት እና የመድሀኒት ምርትን ለማሳደግ የሚውል የ3 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ይፋ አድርጓል፡፡
በማዕከሉ የሀገር ውስጥ አምራቾች አስተባባሪ አቶ አበበ ጌተኑ እንዳሉት÷ 2 ቢሊየን ዶላሩ ከአፍሪኤግዚም ባንክ ቀሪው 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላሩ ደግሞ ከአፍሪካ የክትባቶች ጥምረት (ጋቪ አፍሪካ) የተገኘ ነው።
ድጋፉ የክትባት እና መድሀኒት አምራች ኩባንያዎች የዓለም ጤና ድርጅትን መስፈርት ያሟሉ ምርቶችን እንዲያመርቱ ለማድረግ እንዲሁም አህጉራዊ የክትባት እና መድሃኒት አቅርቦትን ለማሳደግ ያግዛል ብለዋል።
በተጨማሪም ድጋፉ በአፍሪካ ያለውን የመድሀኒት ዋጋ እና ገበያ ለማረጋጋት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ነው ያስገነዘቡት ሲል ስፑትኒክ ዘግቧል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት አህጉራዊ ችግር የሆነውን የክትባት እና መድሀኒት እጥረት ከውጭ ጥገኝነት ለማላቀቅ እየሰሩ ይገኛሉ።
በኢትዮጵያ የተለያዩ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች እና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚሰማሩ ኩባንያዎች መካከል በክትባት እና መድሀኒት አምራችነት የሚሰማሩ እንዳሉ ይታወቃል።
በሚኪያስ አየለ