ኢትዮጵያ ለሰብዓዊ ልማት በሰጠችው ትኩረት ለሁለንተናዊ ብልፅግና መሰረት እየጣለች ነው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ለሰብዓዊ ልማት በሰጠችው ትኩረት ለሁለንተናዊ ብልፅግና መሰረት እየጣለች ነው አሉ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ።
በኢትዮጵያ መንግሥትና በዓለም ባንክ በጋራ የተዘጋጀው የኢትዮጵያ የሰው ሃብት ልማት ፎረም 2025 በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ነው።
አፈ ጉባዔ ታገሰ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ የሀገርን ሁለንተናዊ እድገትና ብልጽግና ለማስቀጠል የሰብዓዊ ልማት ወሳኝ ነው፡፡
የትምህርት፣ ጤና፣ ሥነ ምግብ እና ክህሎትን ማዳበር የሀገራዊ ለውጥ መሠረቶች መሆናቸውን ነው ያብራሩት፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ዘመኑን የዋጀ ብቁ፣ ጤናማና ተወዳዳሪ ትውልድ መገንባት የሚያስችሉ የሰብዓዊ ልማት ሥራዎችን እየተገበረች ትገኛለች ብለዋል፡፡
ከቅድመ መደበኛ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ጥራት ያለው የትምህርት ተደራሽነትን በማስፋት በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ሕጻናትና ወጣቶች በትምህርት ገበታ ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡
የሙያና ክህሎት ተቋማትም በርካታ ተማሪዎችን እያስተናገዱ መሆናቸውን ጠቅሰው ፥ የትምህርት ዘርፍ የሰብዓዊ ልማት ሥራ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን ብቁ ትውልድ የማዘጋጀት ሀገራዊ አጀንዳ መሆኑን ገልጸዋል።
በጤናው ዘርፍም ሁሉን አቀፍ አገልግሎት ለማዳረስ ውጤታማ የጤና ኤክስቴንሽንን በመተግበር ለአፍሪካ ምሳሌ የሚሆን ስኬት አስመዝግበናል ነው ያሉት።
መሰረታዊ የጤና አገልግሎትን በማዳረስ የእናቶችና ህጻናት ሞትን መቀነስ ተችሏል ያሉት አፈ ጉባኤው ፥ በርካታ ሚሊየን ቤተሰቦች የተሟላ የሕክምና አገልግሎት እያገኙ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የተመጣጠነ ሥርዓተ ምግብን በማጠናከር በአካልና በአዕምሮ የዳበረ ትውልድ የመገንባት ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ሰብዓዊ ልማት የኢኮኖሚ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን የሰው ልጆች የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጉዳይ መሆኑንም ተናግረዋል።