የኢትዮጵያ የልማት መርሐ ግብሮች የሚታይ ውጤት እያስመዘገቡ ነው – የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሌማት ትሩፋትን ጨምሮ ኢትዮጵያ የምታከናውናቸው የልማት መርሐ ግብሮች የሚታይ ውጤት እያስመዘገቡ ነው አሉ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ።
ሚኒስትሯ ከዓለም ምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ዋና ዳይሬክተር ኪዩ ዶንግዩ ጋር ተወያይተዋል።
ፋኦ ለኢትዮጵያ ያበረከተውን የእውቅና ሽልማት በተመለከተ ምስጋና ያቀረቡት የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ፤ ኢትዮጵያ የምታከናውናቸው የልማት መርሐ ግብሮች የሚታይ ውጤት እያስመዘገቡ ነው ብለዋል።
በምግብ ራስን ለመቻል ምርታማነትን ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት በተመለከተ ባደረጉት ማብራሪያ፤ የስንዴ ሰብል ልማት እና የሌማት ትሩፋት እንዲሁም የከተማና የገጠር ኮሪደር ልማት ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ስኬታማ መሆኑንም ጨምረው ገልጸው፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት የሚሰሩ የልማት ተግባራት ውጤታማ የሆኑት በደፋር ውሳኔዎች፣ በአመራር ጥበብ እና በኢትዮጵያውያን ታታሪነት ነው ብለዋል።
ፋኦ ኢትዮጵያን በተለያየ መስክ ለማገዝ ቁርጠኛ መሆኑን ማረጋገጡን ሚኒስትሯ ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡