Fana: At a Speed of Life!

በህገወጥ የሐዋላ ገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ላይ ከባድ ርምጃ ይወሰዳል – ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) መንግሥት በህገወጥ የሐዋላ ገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ላይ ከባድ ርምጃ ይወስዳል አሉ፡፡

ባንኩ ከውጭ ሀገር ከሚገኙ ሀዋላ አስተላላፊ ድርጅቶችና ከንግድ ባንኮች ጋር በትብብር መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮችና በሚወሰዱ ህጋዊ ርምጃዎች ዙሪያ ውይይት ተደርጓል።

ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ውይይቱን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ÷ ሐዋላ አስተላላፊ ድርጅቶች በህጋዊ መንገድ እንዲሰሩ መንግስት ድጋፍ በሚያደርግባቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር መደረጉን አንስተዋል፡፡

መንግስት ሁሉም የሐዋላ ገንዘብ አስተላላፊዎች ወደ ህጋዊ መንገድ እንዲገቡ በተደጋጋሚ ያቀረበውን ጥሪ ያልተቀበሉ አንዳንድ ድርጅቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

ብሔራዊ ባንክ በእነዚህ ህገወጥ የሀዋላ ገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ላይ በጥናትና በመናበብ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቀዋል።

እንደ ሀገር የውጭ ምንዛሪ ሀብት መኖሩን ያነሱት ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)÷ ብሔራዊ ባንክ በአስተማማኝ ሁኔታ ይህን ሀብት እያቀረበ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

የሐዋላ ገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች በበኩላቸው፥ ህጋዊ አካሄድን ይዞ ለመንቀሳቀስ እንዲያስችላቸው ከመንግሥት እንዲደረግላቸው የሚፈልጉትን ዝርዝር ነጥቦች አንስተዋል።

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.