ኢትዮጵያን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የተጀመረውን ጉዞ በጋራ ከዳር ማድረስ ይገባል – አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የተጀመረውን ጉዞ በጋራ ከዳር ማድረስ ይገባል አሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2017 ዓ.ም የበጎ ፈቃደኞች አገልግሎት የእውቅናና የሽልማት መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡
አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በመላ ሀገሪቷ በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በየዘርፉ በጎ ፈቃደኝነትን ለማስረፅ የሚያደርገው ጥረት በእጅጉ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በጎ ፈቃደኝነት የሀገር ፍቅር አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፥ መንግስት በዚህ በጎ ተግባር በመሳተፍ ሀገራቸውንና ህዝባቸውን በቀናነት ላገለገሉ አካላት ምስጋና ያቀርባል ነው ያሉት፡፡
በጎነት በአንድነት መኖርና በአንድነት ማደግ ነው ያሉት አፈ ጉባኤው፥ ኢትዮጵያን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የተጀመረውን ጉዞ በጋራ ከዳር ማድረስ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በቀጣይም ሁሉም ዜጋ ለበጎ ስራ መተባበር እንዳለበት ገልጸው፥ በዚህም የኢትዮጵያን የማንሰራራት ዘመን እውን ለማድረግ መተባበር ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡