የገጠሩን ማሕበረሰብ ኑሮ ለመቀየር የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል – አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የገጠሩን ማሕበረሰብ ኑሮ የመቀየር እና ምርታማነትን የማሳደግ ተግባር የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ባጠረ ጊዜ ማሳካት ያስችላል አሉ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ትናንት በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን የክረምት ስንዴ ምርት አሰባሰብን ጎብኝተው የበጋ ስንዴ እርሻ ሥራን አስጀምረዋል፡፡
አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ከጉብኝቱ በኋላ በሰጡት አስተያየት÷የገጠሩን ማሕበረሰብ ኑሮ የመቀየር ሥራ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና በአጭር ጊዜ ማሳካት የሚያስችል ነው ብለዋል።
መንግስት ከተሞችን የመቀየር እና ለነዋሪዎች ምቹ የማድረግ እንዲሁም የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማሳደግ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ አብዛኛው ማሕበረሰብ የሚኖረው በገጠር ክፍል በመሆኑ መንግስት በገጠር የሚኖሩ ዜጎችን ኑሮ ለመቀየር እና ምርታማነት ለማሳደግ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
በገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል በአትክልት፣ ፍራፍሬና ሰብል እጅግ አበረታች ውጤት መገኘቱንና የምስራቅ ሸዋ ዞን የስንዴ ምርት ሥራ የሚያመላክተው ይህንኑ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
በዞኑ ያለው የኩታ ገጠም የስንዴ እርሻ በኮምባይነር እየታጨደ መሆኑን ጠቁመው÷ ይህም ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ስንዴ፣ ሩዝ እና አቮካዶን ጨምሮ በተለያዩ ምርቶች ራሷን ለመቻል እያከናወናቸው ያለው ሥራ አመርቂ ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ ስንዴ ከመግዛት ተላቃ በራሷ የማምረት አቅምን ማሳደጓ የዚሁ ሥራ ማሳያ መሆኑን ጠቁመው ÷ የተጀመረውን ሥራ አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ነው ያሉት፡፡
በኦሮሚያ ክልል በገጠር ትራንስፎርሜሽን እየተከናወነ ያለው ሥራ በሌሎች ክልሎችም እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት አፈ ጉባዔው÷ ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ያለው ሥራ ውጤታማ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የገጠሩን ክፍል ለመቀየር እየተከናወነ ያለው ሥራ አበረታች መሆኑንና ተደራሽነቱን በማስፋት የኢትዮጵያን ብልጽግና በአጠረ ጊዜ እንደሚሳካ አያጠራጥርም ነው ያሉት።