Fana: At a Speed of Life!

አሁን ያለውን እድል ከምናበላሽ በትብብር መንፈስ ብንሰራ የእኛና የልጆቻችን ነገ ያማረ ይሆናል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አሁን ያለውን እድል ከምናበላሽ በትብብር መንፈስ ብንሰራ የእኛም ሆነ የልጆቻችን ነገ ያማረ ይሆናል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው የታደሰውን የፋሲል አብያተ መንግሥት ጊቢ መርቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ዜጎች ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ ተንቀሳቅሰው የሀገራቸውን ልማት ማየትና ማገዝ እንዲችሉ ሰላም ያስፈልጋል፡፡

ለአብነትም ከጎንደር ጎርጎራ ለመሄድ ጎንደሬዎች በወታደር ተጠብቀው እንዴት ልማት ሊሰራ ይችላል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

እዚህ አካባቢ የወጡ ወንድሞቻችን ጊዜ ሳያባክኑ ተመልሰው በትብብርና በአንድነት ሀገር ማልማት እና መስራት ላይ ቢያተኩሩ ሲሉ መክረዋል፡፡

ዛሬ ጎንደርን፣ ባሕርዳርን ወይም አማራ ክልልን ከአማሮች በስተቀር ማንም አያዝዝበትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ እኛ ሲፈቀድልን እንደ እድል ወስደን ከማገዘ በስተቀር በእለት ተዕለት ጉዳዮችና ሥራዎች ውስጥ እጃችንን አናስገባም ብለዋል፡፡

ይህ እድል ኢትዮጵያ ውስጥ አልነበረም፤ አሁን ከምናበላሽ በትብብር መንፈስ ብንሰራ የእኛ እና የልጆቻችን ነገ ያማረ ይሆናል ነው ያሉት፡፡

ስለሆነም በትብብር መንፈስ ዳግም ባሕርዳር፣ ጎንደር፣ አማራ እንዲሁም ኢትዮጵያ እንዲወለዱ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ጎንደር ጥንታዊና ታሪካዊ ሁነቷን ሳትለቅ ዳግም እስክትወለድና በዓለም አሸብራቂ ከተማ እስክትሆን ድረስ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ጉልበት ይሸሻል፣ ጊዜ ይሸሻል፣ ስልጣን ይሸሻል፣ ሁሉ አላፊ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ( ዶ/ር)÷ የማያልፈው እንደዚህ ያለው ታላቅ ሥራ ነው፤ ታላቅ ሥራ በጋራ እንስራ ሲሉ አጽንኦ ሰጥተዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.