Fana: At a Speed of Life!

የቱርክ ቀዳማዊት እመቤት ቤተሰብን የሚያጠናክር ዓለም አቀፋዊ የፖሊሲ ርምጃ እንዲወሰድ ጠየቁ

‎አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቱርክ ቀዳማዊት እመቤት ኤሚን ኦርዶኻን የቤተሰብ ሁኔታን የሚያጠናክር ዓለም አቀፋዊ የፖሊሲ ርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል፡፡

ቀዳማዊት እመቤቷ “ግሮዊንግ ዩሮፕ 2025” በተባለው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት÷ የዓለም ህዝቦች የቤተሰብ ሁኔታ አደጋ ላይ መውደቁን አስገንዝበዋል።

ሰለጠነ በሚባለው ዓለም በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ተሰባስበው በዓላትን በጋራ የሚያሳልፉ ብዝሃ ቤተሰብ እየጠፉ መጥተዋል ነው ያሉት።

ይህ ሁኔታ ያለንበት ዓለም የባህል ለውጥ ብቻ ሳይሆን ዓለም ዋና ማህበራዊ መሰረት ከሆነው ቤተሰብ ራሱን እያገለለ መሆኑን የሚያሳይ ምልክት መሆኑን አብራርተዋል።

በዓለም የአንዲት እናት አማካኝ የመውለድ ምጣኔ 2 ነጥብ 2 በመቶ መሆኑን ጠቅሰው÷ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የዓለም ሀገራት አሁን ያለውን ትውልድ መተካት ከሚችሉበት ደረጃ በታች መሆናቸው አሳሳቢ እንደሆነ ተናግረዋል።

እስከ ፈረንጆቹ 2030 ከስድስት ሰዎች አንዱ እድሜው ከ60 በላይ ሊሆን እንደሚችል በመጥቀስ በፈረንጆቹ 2050 ደግሞ እድሜያቸው ከ80 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ቁጥር በሶስት እጥፍ ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመላክተዋል፡፡

ይህም በዓለም አቀፉ ስነ ህዝብ ላይ የአዲስ ትውልድ ክፍተትን ሊፈጥር ይችላል  ማለታቸውን ቲአርቲወርልድ ዘግቧል፡፡

እያንዳንዱ ውልደት ለመጪው ዓለም አዲስ ነገር ይጨምራል ያሉት ቀዳማዊት እመቤት ኤሚን ኤርዶኻን÷ የውልደት መጠን እና የወጣቶች ቁጥር መቀነስ የዓለምን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እድገት ያዛባል ብለዋል፡፡

ይህንን ችግር ለመከላከል ቱርክ እየሰራች መሆኑን በመጠቀስ፤ የቤተሰብ ሁኔታን ለማሻሻል የሚያስችሉ ተግባራት በፖሊሲ ተደግፈው እየተከናወኑ እንደሆነ ተናግረዋል።

የቤተሰብ ሕይወት ግቦችን ለማሳካት እንቅፋት ይሆናል የሚል የተዛባ አስተሳሰብ ቤተሰብን በመተው ግላዊነትን ከፍ ለማድረግ ያለመ ነው ሲሉ ኮንነዋል፡፡

በመሆኑም ዓለም ቤተሰብን ማዕከል ፖሊሲዎችን ተግባራዊ በማድረግ ችግሩን ለመከላከል በቁርጠኝነት እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.