የመከላከያ ሪፈራል ሆስፒታል አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመከላከያ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታልን አገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመን እየተሰራ ነው አሉ የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሃመድ (ኢ/ር)፡፡
አይሻ መሃመድ (ኢ/ር) እና የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በቢሸፍቱ የመከላከያ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታልን ጎብኝተዋል፡፡
በጉብኝታቸውም የሆስፒታሉ የንጽሕና አስተዳደር ሥርዓት ደረጃ ለመጠበቅና ለማዘመን እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡
በአንድ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ የሆስፒታሉን የላውንደሪና የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓት በማዘመንና ተግባራዊ ስልጠና በመስጠት ሥራውን ለማሳለጥ የተደረገውን ጥረት አድንቀዋል፡፡
ሥራው የሆስፒታሉን አጠቃላይ የመገልገያ አልባሳት፣ የታካሚ ልብሶችና ቁሳቁስ እንዲሁም ሙሉ የንጽህ አጠባበቅ ሒደቱን ዘመናዊና ከዓለም አቀፍ ደረጃ ጋር በማጣጣም የደህንነት መስፈርቶችን እንዲያሟላ ለማድረግ ያግዛል፡፡
ሆስፒታሉ ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ አገልግሎት እንዲሰጥና የኢንፌክሽን መከላከል አቅሙን ይበልጥ የሚያሻሽል መሆኑም ተመላክቷል፡፡
የመከላከያ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል በኢትዮጵያ ውስጥ ልዩ የሕክምና አገልግሎቶችን በመስጠት ረገድ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡
አሁን የተዘረጋው ዘመናዊ የንጽሕና አጠባበቅ ሥርዓትም የታካሚዎችን ደህንነት ይበልጥ በማሻሻል ከሀገር ውጭ የሚደረግ የሕክምና ጉዞን በመቀነስ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።
በጉብኝት መርሐ ግብሩ ጄኔራል መኮንኖች፣ ከፍተኛ የሕክምና ባለሙያዎችና የሆስፒታሉ ሰራተኞች መሳተፋቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡
በመላኩ ገድፍ