በቡድን 20 የመሪዎች ጉባኤ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስጠብቁ ውይይቶች ተደርገዋል – አቶ አህመድ ሺዴ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ አፍሪካ ከተካሄደው በቡድን 20 የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስጠብቁ የሁለትዮሽ ውይይቶች ተደርገዋል አሉ የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ ጉባኤውን አስመልከተው በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት÷ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመራው ልዑክ ከስብሰባው ጎን ለጎን ከተለያዩ ሀገራት መሪዎችና የባለብዙ ወገን ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ስኬታማ ውይይት አድርጓል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ከደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ጋር ባደረጉት ውይይት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነቶች የሚያጠናክሩ ምክክሮች ተደርገዋል ነው ያሉት፡፡
እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጀርመን፣ እንግሊዝ፣ ብራዚል፣ ቱርክ፣ ኢንዶኖዥያ፣ፈረንሳይ፣ ህንድ እና ጣሊያን መሪዎች ጋር ባደረጓቸው የተናጠል ውይይቶች ኢትዮጵያ ከሀገራቱ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተባበሩት መንግስታት ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ፣ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጂኦርጂየቫ፣ ከዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት አጄይ ባንጋ፣ ከአውሮፓ ኅብረት ም/ቤት ፕሬዚዳንት አንቶኒዮ ኮስታ እና ከተለያዩ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ጋር መወያየታቸውን ተናግረዋል፡፡
ልዑኩ በቆይታው የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስከብሩ የተለያዩ ስኬታማ የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ውይይቶችን አድርጓል ነው ያሉት፡፡
በተለይም በጤናው ዘርፍ የሚደረገው ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሀገራትን በመወከል በመድረኩ ድምጿን ማሰማቷን ገልፀዋል፡፡
በመድረኩ ዓለም አቀፉ የጤና ድጋፍ ተቋም የሆነው ግሎባል ፈንድ ለአፍሪካ ሀገራት 11 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል ያሉት ሚኒስትሩ÷ ድጋፉ ሰፊ የጤና ፕሮግራም ላላት ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ