በመዲናዋ የመኖሪያ ቤት ጥያቄን ለመመለስ በትኩረት እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዜጎችን የቤት ባለቤት ለማድረግና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራሁ ነው አለ።
አስተዳደሩ በመንግሥት፣ በበጎ ፈቃድ እና በግል ገንቢዎች ትብብር በርካታ ቤቶችን በመገንባት ዜጎች በፍትሃዊነት ተጠቃሚ መሆናቸውን አመላክቷል።
በዚህም በተለያዩ አማራጮች ቤቶችን በመገንባት፣ የመኖሪያ ቤት አቅርቦትን በማሻሻል አመርቂ ውጤቶች ስለመገኘታቸውም ጠቁሟል።
አስተዳደሩ ከግል ባለሀብቶች ጋር በቅንጅት በመስራት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የቤት ፍላጎት ለማሟላትና ተደራሽ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እየሰራ እንደሆነም አስታውሷል።
እስካሁን ድረስ በኮንዶሚኒየም መርሐ ግብር 139 ሺህ 8 ቤቶች፣ ለአቅመ ደካሞች እና ለሀገር ባለውለታዎች 40 ሺህ 576 ቤቶች፣ በከተማ አስተዳደሩ የተገነቡ የኪራይ ቤቶች 24 ሺህ 819 እንዲሁም በሪል ስቴት፣ በማህበር እና በግል ገንቢዎች 175 ሺህ 605 ቤቶች መገንባታቸውን ገልጿል።
በዚህም ከ380 ሺህ በላይ ቤቶችን ለተጠቃሚዎች መተላለፋቸውን የገለጸው የከንቲባ ጽህፈት ቤት መረጃ፤ በቀጣይም የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም የዜጎችን የመኖሪያ ቤት ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጧል።