ብሪኤግዚት የብሪታኒያ ጠቅላላ ምርት 8 በመቶ እንዲቀነስ ማድረጉን ጥናት አመለከተ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ብሪታኒያ ከአውሮፓ ህብረት መውጣቷን ተከትሎ ዓመታዊ ጥቅል ምርቷ እስከ 8 በመቶ መቀነሱን ጥናቶች አመላከቱ፡፡
የዩኬ ማዕከላዊ ባንክ የኢኮኖሚ ባለሙያን ጨምሮ አምስት የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይፋ ባደረጉት ጥናት መሰረት ብሪታኒያ ከአውሮፓ ህብረት ከወጣች ወዲህ በአምስት ዓመታት ውስጥ ዓመታዊ ጥቅል ምርቷ ከ6 እስከ 8 በመቶ ዝቅ ብሏል፡፡
በተጨማሪም የሀገሪቱ ኢንቨሰትመንት ከ12 እስከ 18 በመቶ፣ የስራ እድል ፈጠራን እንዲሁም የአምራች ዘርፉን ምርት በተመሳሳይ ከ3 እስከ 4 በመቶ እንዲቀንስ ማድረጉ ነው የተገለጸው፡፡
በተጨማሪም የሀገሪቱ ኩባንያዎች ሸቀጦችን ለማምረትና አገልግሎቶችን ለመስጠት ያላቸው ፍላጎት እንዲሁም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኢንቨሰትመንት እየቀነሰ መምጣቱ በጥናቱ ተመላክቷል፡፡
ብሪታኒያ ከአውሮፓ ሀብረት መውጣቷ በኢኮኖሚዋ ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩን የአሜሪካውን ብሔራዊ የኢኮኖሚ ጥናት ቢሮ ጠቅሶ አናዶሉ ኤጀንሲ ዘግቧል፡፡
ብሪታኒያ በፈረንጆቹ 2016 ባካሄደችው ድምጸ ውሳኔ መሰረት ከአውሮፓ ኅብረት ለመውጣት ውሳኔ ያሳለፈች ሲሆን፥ በፈረንጆቹ 2020 በይፋ ከአውሮፓ ህብረት ጋር መለያየቷ ይታወሳል፡፡
በሚኪያስ አየለ