Fana: At a Speed of Life!

በሴቶችና ሕጻናት ላይ የሚፈጸምን ጥቃት የማይታገስ ማሕበረሰብ ለመፍጠር…

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሴቶችና ሕጻናት ላይ የሚፈጸምን ማንኛውንም አይነት ጥቃት የማይታገስ ማሕበረሰብ ለመፍጠር ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል አሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፡፡

ሚኒስትሯ በዓለም ለ34ኛ ጊዜ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ20ኛ ጊዜ እየተከበረ የሚገኘውን 16ቱ ቀናት ዓለም አቀፍ የጸረ ጾታዊ ቀን አስመልክተው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም በሴቶችና ሕጻናት ላይ የሚደርስ ጥቃት በአካላዊና አእምሯዊ ጤንነትና ደህንነት እንዲሁም በሁሉም የሕይወታቸው ደረጃ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር አስረድተዋል፡፡

በቤተሰብ፣ በሕብረተሰብ እንዲሁም በሀገር ላይ መጠነ ሰፊ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በማስከተል ዘላቂ ልማት እንዳይረጋገጥ እንቅፋት እንደሚፈጥርም አብራርተዋል፡፡

ለዚህም ሚኒስቴሩ ጥቃትን ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ አሰራሮችንና የአገልግሎት ሥርዓቶችን በመዘርጋት በቁርጠኝነት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

በተለይም በተጎጂዎች ላይ የሚደርሰውን የጤና፣ የማሕበራዊና ሥነ ልቦናዊ እንዲሁም የሕግ ምላሽ ክፍተቶችን ለመቅረፍ እየሰራ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

የዘንድሮው ንቅናቄ የዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም በሴቶችና ሕጻናት ላይ የሚደርስን ጥቃት መከላከልና ማስቆም ላይ ትኩረት በማድረግ በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡

ንቅናቄው ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለመከላከል፣ ተጋላጭነት ለመቀነስ፣ ለተጎጂዎች ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግና የጾታ ጥቃትን ለማስወገድ ያለመ ነው ብለዋል፡፡

በዚህ መሰረትም በሁሉም ዩኒቨርስቲዎችና ት/ቤቶች፣ የሐይማኖት ተቋማት፣ በግል ተቋማትና ኢንዱስትሪዎች፣ በመንግስት መስሪያ ቤቶች እና ሌሎች ቦታዎች ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በሴቶችና ሕጻናት ላይ የሚደርሰው ጥቃት በአብዛኛው በቅርብ ሰዎች የሚፈጸም መሆኑን ጠቁመው ÷ ጾታዊ ጥቃትን የማይታገስ ማሕበረሰብ ለመፍጠር ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የንቅናቄ መርሐ ግብሩን በስኬት ለማጠናቀቅ በፌደራልና በክልሎች የተለያዩ ኮሚቴዎች ተዋቅረው እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.