Fana: At a Speed of Life!

ወደ ቀደመ ብቃቱ እየተመለሰ የሚገኘው ፎደን…

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) እንግሊዛዊው የፊት መስመር ተጫዋች ፊል ፎደን በውድድር ዓመቱ ድንቅ እንቅስቃሴ በማሳየት ወደ ቀድሞ ብቃቱ እየተመለሰ ይገኛል፡፡

ከ2017/18 ጀምሮ ለማንቼስተር ሲቲ እየተጫወተ የሚገኘው ፎደን ስድስት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ እና የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግን ጨምሮ የተለያዩ ዋንጫዎችን አሳክቷል፡፡

ማንቼስተር ሲቲ በተከታታይ ለአራት ዓመታት የሊጉን ዋንጫ እና በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን ሲያሳካ ከቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነበር፡፡

በተለይም በ2023/24 የውድድር ዘመን ፎደን በእግር ኳስ ሕይወቱ ምርጡን ጊዜ ያሳለፈ ሲሆን ÷ በሊጉ በ35 ጨዋታዎች 19 ግቦችን አስቆጥሮ 8 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻቶ ማቀበሉ አይዘነጋም፡፡

በዚያው ዓመት በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ውድድር በስምንት ጨዋታዎች በአጠቃላይ 9 ግቦች ላይ በቀጥታ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡

በዓመቱ ከሲቲ ጋር የሊጉን ዋንጫ ከማሳካት ባለፈ የፕሪሚየር ሊጉ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ የተመረጠ ሲሆን ÷ በ2020/21 እና በ2021/22 የውድድር ዓመት በተከታታይ የሊጉን ወጣት ተጫዋች ሽልማት አሸንፏል፡፡

ማንቼስተር ሲቲ የሊጉን ዋንጫ በተነጠቀበት በ2024/25 የውድድር ዘመን ፊል ፎደን ደካማ ጊዜ ማሳለፉ የሚታወስ ነው፡፡

አምና ወጥ ብቃት ማሳየት ባለመቻሉ ብዙ ትችት እየተሰነዘረበት የውድድር ዘመኑን ያጠናቀቀው ፎደን በዚህ ዓመት ግን ወደቀድሞ ብቃቱ በመመለስ ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል፡፡

በዚህ የውድድር ዓመት ለማንቼስተር ሲቲ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ የፎደን አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ነው፡፡

የ25 ዓመቱ ተጫዋች በ2025/26 የውድድር ዓመት ለማንቼስተር ሲቲ በሁሉም ውድድሮች እስካሁን ባደረጋቸው 19 ጨዋታዎች 9 ግብ አስቆጥሮ 4 ለግብ የሚሆን ኳስ አመቻችቶ አቀብሏል፡፡

በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በሁሉም ውድድር ማስቆጠር የቻለው 10 ግብ ሲሆን ÷ አመቻችቶ ያቀበለው ደግሞ 3 ብቻ ነው፡፡

በ2023/24 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ እና የማንቼስተር ሲቲ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ ያጠናቀቀው ፎደን በቀጣዩ ዓመት ግን ደካማ ጊዜ ነበር ያሳለፈው፡፡

በዚህ ዓመት ካለፈው የውድድር ዘመን ራሱን በሚገባ አሻሽሎ በመምጣት መልካም የውድድር ዓመት ጅማሮ ላይ ይገኛል፡፡

በዚህ ወቅት ከኤርሊንግ ብራውት ሃላንድ ቀጥሎ ለማንቼስተር ሲቲ የዋንጫ ተፎካካሪነት ፊል ፎደን የማይተካ ሚና እየተጫወተ ነው፡፡

ሀገሩ እንግሊዝን ከ16 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ጀምሮ ያገለገለው ፎደን ከፈረንጆቹ 2020 ወዲህ ዋናውን ብሔራዊ ቡድን እያገለገለ ይገኛል፡፡

በቀጣይ በአሜሪካ፣ካናዳ እና ሜክሲኮ አዘጋጅነት በሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ለሀገሩ ጥሪ እንዲቀርብለት ይህንን ወጥ ብቃቱን እያሳየ መቆየት ይጠበቅበታል፡፡

47 ቁጥር ማልያ ለብሶ የሚጫወተው ፊል ፎደን ቁጥሩን የመረጠበት ምክንያት በ47 ዓመታቸው ሕይወታቸው ላለፉት አያቱ ሮኒ ክብር ሲል መሆኑን በአንድ ወቅት ገልጿል፤ ከዚህ ባለፈም 47 ቁጥርን አንገቱ ላይ ተነቅሷል፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.