አስቶን ቪላን ወደቀደመ ታሪኩ እየመለሱት የሚገኙት ኡናይ ኢምሬ…
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አስቶን ቪላን ወደቀደመ ከፍታው እየመለሱ በሚገኙት አሰልጣኝ ኡናይ ኢምሬ ደማቅ ድሎችን እየተቀዳጁ ደስታን በማጣጣም ላይ የሚገኙት የክለቡ ደጋፊዎች “የምንፈልገውን የሚያውቅ ምርጥ አሰልጣኝ አግኝተናል” የሚል መልዕክት ያለው ሕብረ ዜማቸው የቪላ ፓርክ ማድመቂያ ሆኗል፡፡
የምዕራብ ሚድላንዱ ክለብ አስቶን ቪላ በቀደሙት ዓመታት በእንግሊዝ እግር ኳስ ታሪክ በዋንጫዎች የታጀበ ስኬታማ ጊዜያትን ማሳለፍ ችሏል፡፡
ሰባት ጊዜ የሊጉ ሻምፒዮን ሲሆን ፥ በተመሳሳይ ሰባት ጊዜ የኤፍ ኤ ዋንጫን ማሳካት ችሏል፤ ከሀገር ውስጥ ውድድር ባሻገር በፈረንጆቹ 1981/82 የውድድር ዓመት የአውሮፓ ሻምፒዮን ሆኗል፡፡
ይሁን እንጂ በኋለኞቹ ዓመታት ከከፍታው እየወረደ ከፕሪሚየር ሊጉ ተሳትፎ ባለፈ በዋንጫ ተፎካካሪነት ለመቀጠልም ሆነ በአህጉራዊ ውድድሮች ተሳትፎውን ለማረጋገጥ ተቸግሮ ቆይቷል፡፡
በፈረንጆቹ 2022 በወቅቱ የአስቶን ቪላ አሰልጣኝ የነበረውን የቀድሞውን የሊቨርፑል አማካይ ስቴቨን ጄራርድ ተክተው አስቶን ቪላን የተረከቡት ስፔናዊው አሰልጣኝ ኡናይ ኢምሬ ግን ክለቡን ወደ ቀደመው ውጤታማ ጊዜ እየመለሱት ይገኛሉ፡፡
ከአስቶን ቪላ አስቀድሞ ሌላኛውን የእንግሊዝ ክለብ አርሰናልና የፈረንሳዩን ሀያል ክለብ ፒኤስጂ ጨምሮ በርካታ የስፔን ክለቦችን ማሰልጠናቸው ይታወሳል፡፡
ኡናይ ኢምሬ የአሰልጣኝነት ስራን የጀመሩት በተጫዋችነት ባሳለፉበት የስፔኑ ክለብ ሎርካ ዲፖርቲቫ ነበር፡፡ በስፔን በ3ኛው የውድድር እርከን ላይ በሚሳተፈው ሎርካ ዲፖርቲቫ በተጫዋችነት ያሳለፉ ሲሆን ፥ በጉዳት ምክንያት ከተጫዋችነት ራሳቸውን ሲያገልሉ ክለቡን እንዲመሩ በተሰጣቸው ኃላፊነት ነበር ወደ አሰልጣኝነት ሕይወት የገቡት፡፡
በመጀመሪያ ዓመት የአሰልጣኝነት ስራቸው ክለቡን ወደ ላይኛው ሊግ ማሳደጋቸው ደግሞ በአሰልጣኝነት ለመቀጠል ይበልጥ መነሳሳት እንደፈጠረላቸው ይነገራል፡፡
በኋላም በፈረንጆቹ 2006 ሌላኛውን የስፔን ክለብ አልሜሪያ በመረከብ ክለቡን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ላሊጋ በማሳደግ በመጀመሪያው ዓመት የሊጉ ቆይታው 8ኛ ደረጃን ይዞ እንዲያጠናቅቅ አስችለዋል፡፡
በመቀጠልም በፋይናንስ ችግርና በውጤት ማጣት ውስጥ የነበረውን ሌላኛውን የላሊጋ ክለብ ቫሌንሺያ ተረክበው በ4 ዓመታት ውስጥ ለሦስት ጊዜ በሊጉ 3ኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ ክለቡን ለተከታታይ ዓመታት የሻምፒየንስ ሊግ ተሳታፊ አድርገውታል፡፡
በፈረንጆቹ 2012 ወደ ሩሲያ በማቅናት ስፓርታክ ሞስኮን ማሰልጠን የጀመሩ ሲሆን ፥ በውጤት ማጣት ምክንያት ከክለቡ ጋር ሲለያዩ ዳግም ወደ ስፔን ተመልሰው በ2012/13 የውድድር ዓመት አጋማሽ ሴቪያን ተረከቡ፡፡
በዚያው ዓመት ክለቡ በላሊጋው 5ኛ ደረጃን ይዞ እንዲያጠናቅቅ አስችለዋል፡፡ በሴቪያ ቆይታቸው ከ2013/14 እስከ 2015/16 ለሦስት ተከታታይ የውድድር ዓመት የስፔኑን ክለብ የዩሮፓ ሊግ ሻምፒዮን ማድረግ ችለዋል፡፡
በኋላም የፈረንሳዩን ሀያል ክለብ ፒኤስጂ በመረከብ በፓሪሱ ክለብ የሁለት ዓመታት ቆይታቸው ክለቡን በ2017/18 የሊግ-1 ሻምፒዮን ከማድረጋቸው በተጨማሪ ከክለቡ ጋር ሁለት ጊዜ የፈረንሳይ ዋንጫ፣ ሁለት ጊዜ የፈረንሳይ ሊግ እንዲሁም ሁለት ጊዜ የፈረንሳይ ሱፐር ካፕ ዋንጫዎችን አሸንፈዋል፡፡
ከፈረንሳዩ ክለብ ፒኤስጂ ጋር ከተለያዩ በኋላ ወደ እንግሊዝ በመምጣት የሰሜን ለንደኑን ክለብ አርሰናል ተረክበዋል፡፡ 22 ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ መድፈኞቹን የመሩትን አርሰን ቬንገር በመተካት ለንደን የደረሱት ስፔናዊው አሰልጣኝ ከ18 ወራት የኤሚሬትስ ቆይታቸው በኋላ ተሰናብተዋል፡፡
አርሰናል በ2018/19 የውድድር ዓመት በአሰልጣኝ ኡናይ ኢምሬ እየተመራ በሊጉ 5ኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅ ለዩሮፓ ሊግ ፍጻሜ መድረስ ችሎ ነበር፡፡ ሆኖም በፍጻሜው በቼልሲ 4 ለ 1 ተሸንፎ ዋንጫውን ማሸነፍ ሳይችል ቀርቷል፡፡
ከአርሰናል በተሰናበቱበት መንገድ ደስተኛ እንዳልሆኑ ደጋግመው የሚናገሩት ስፓኒያርዱ አሰልጣኝ በሌሎች ክለቦች የነበራቸውን ድጋፍ ከአርሰናል እንዳላገኙና ባይተዋርነት እንደተሰማቸው ገልጸው ነበር፡፡
ከአርሰናል ስንብታቸው በኋላ ወደ ስፔን ተመልሰው የላሊጋውን ክለብ ቪያሪያል የተረከቡ ሲሆን፥ በዚያው ዓመት በዩሮፓ ሊግ በግማሽ ፍጻሜ የቀድሞ ክለባቸውን አርሰናልን እንዲሁም በፍጻሜው ማንቼስተር ዩናይትድን በማሸነፍ ዋንጫውን ማሳካት ችለዋል፡፡
ቪያሪያል በኡናይ ኢምሬ እየተመራ በቀጣዩ የውድድር ዓመት በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ እስከ ግማሽ ፍጻሜ መጓዝ ችሎም ነበር፡፡
ዳግም ወደ እንግሊዝ በመመለስ አስቶን ቪላን በተረከቡበት ዓመት ክለቡ ከ13 ዓመታት በኋላ ወደ አውሮፓ መድረክ እንዲመለስ አስችለዋል፡፡ በዩሮፓ ሊግ እስከ ግማሽ ፍጻሜ እንዲጓዝ ከማስቻላቸው ባለፈ ክለቡን ከ40 ዓመታት በኋላ ወደ ሻምፒየንስ ሊግ በመመለስ እስከ ሩብ ፍጻሜ መጓዝ ችለዋል፡፡
ኢምሬ አስቶን ቪላን ከተረከቡ ወዲህ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ሻምፒየንስ ሊግን ጨምሮ ክለቡ በቋሚነት በአውሮፓ መድረክ ተሳታፊ ለመሆን በቅቷል፡፡
በዘንድሮው የውድድር ዓመት አጀማመሩ ጥሩ ባይሆንም ተከታታይ ድል በማስመዝገብ በሊጉ 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን ፥ በተመሳሳይ በዩሮፓ ሊግ 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
የቪላን ስኬታማ ጉዞ እየመሩ የሚገኙት የ54 ዓመቱ ስፔናዊ አሰልጣኝ ክለቡን በተለይም በፕሪሚየር ሊጉ የዋንጫ ፉክክር እስከምን ድረስ ይዘውት ይዘልቃሉ የሚለው ተጠባቂ ነው፡፡
የጨዋታን ሚዛን መጠበቅ፣ ከኳስ ቁጥጥር ይልቅ ሁሉንም የሜዳ ክፍል መቆጣጠር፣ በኃይል ተጭኖ ኳስን መንጠቅና በታክቲካዊ የቦታ አጠባበቅ ላይ የተመሰረተ የቡድን ጨዋታ ኡናይ ኢምሬ በስፋት የሚታወቁበት የእግር ኳስ ፍልስፍና መሆኑ ይነገራል።
በሁሉም ውድድሮች ያለፉትን ዘጠኝ ጨዋታዎች በማሸነፍ አስደናቂ ጉዞ ላይ በሚገኘው ቡድናቸው ደስተኛ የሆኑት የቪላ ደጋፊዎችም “የምንፈልገውን የሚያውቅ ምርጥ አሰልጣኝ አግኝተናል” በሚለው ሕብረ ዜማቸው የቪላ ፓርክ ተጨማሪ ድምቀት ሆነው ቀጥለዋል፡፡
በኃይለማሪያም ተገኝ