98 በመቶ የመንግሥት አገልግሎቶችን በኦንላይን ለመስጠት በትኩረት ይሰራል – ፍሬሕይወት ታምሩ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2030 ዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ 98 በመቶ የሚሆኑትን የመንግሥት አገልግሎቶች በኦንላይን ለመስጠት በትኩረት ይሰራል አሉ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ፡፡
ፍሬሕይወት ታምሩ የ2030 ዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂን ለመተግበር ኢትዮጵያ ያላትን አስቻይ ሁኔታና ሌሎች ጉዳዮች አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸውም ትስስር፣ ዲጂታል መሰረተ ልማት እና ፕላትፎርም እንዲሁም ኤሌክትሪክ ለአንድ ሀገር አካታች፣ ተደራሽና ፈጣን ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ወሳኝ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ባለፉት አምስታ ዓመታት ኢትዮጵያ በዲጂታል 2025 በርካታ ውጤቶች ማስመዝገቧን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ አስረድተዋል፡፡
ለአብነትም በ1 ሺህ 30 ከተሞች የ4ጂ ኢንተርኔት ተደራሽ መሆኑን ገልጸው÷የሞባይል ደንበኞች ቁጥርን 97 ሚሊየን መድረሱንና 57 ሚሊየን የሚሆኑት የኢንተርኔት ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
እያንዳንዱ ዜጋ ከተስፋፋው የዲጂታል ኢኮኖሚ ትሩፋት ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል የሥማርት ስልክ ተደራሽነትን ለማሳደግ በተከናወነ ሥራ 46 በመቶ ማድረስ መቻሉን አንስተዋል፡፡
አሁን ላይ ከ22 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የፋይበር አቅም እንዲሁም በከተሞች 900 ሺህ ደንበኞችን ያስተሳሰረ 14 ሺህ ሜትሮ ፋይበር መኖሩን አመልክተዋል፡፡
ከሞባይን ባንኪንግ ሥርዓት ጋር ተያይዞ አሁን ላይ ቴሌ ብርን ጨምሮ በሌሎች የተከፈቱ አካውንቶች ቁጥር ወደ 161 ሚሊየን መድረሱን ነው የተናገሩት፡፡
የኤሌክትሪክ አቅምን ከማሳደግ አንጻርም ኦፍ ግሪድና ሶላርን ሳይጨምር ከ54 በመቶ በላይ ተደራሽ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል፡፡
በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የሞባይል ተጠቃሚ ደንበኞችን ቁጥር 128 ሚሊየን ለማድረስና የ5ጂ ኔትወርክ ሽፋንን በ100 ከተሞች ተደራሽ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል፡፡
በ2030 የዲጂታል ክፍያን ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት አንጻር አሁን ካለበት ከ7 እጥፍ በላይ ለማሳደግ በልዩ ትኩረት ይሰራልም ነው ያሉት።
98 በመቶ የሚሆኑትን የመንግሥት አገልግሎቶች በኦንላይን ለመስጠት እና የጂዲፒውን 750 በመቶ በዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ለመፈጸም እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡
በስትራቴጂው አካታች፣ ፈጣን እና ተደራሽ ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Facebook https://web.facebook.com/fanasport
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!