Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በስትራቴጂ የሚመራ ዘላቂ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት እየሰራች ነው – ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በስትራቴጂ የሚመራ ዘላቂ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት እየሰራች ነው አሉ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)፡፡

በኢትዮጵያ ብክለት ቀናሽ እንቅስቃሴ 2025 ኤግዚቢሽን እና ፎረም በዛሬው እለት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት ተጀምሯል፡፡

ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት÷ኤግዚቢሽን እና ፎረሙ ኢትዮጵያ ወደ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለምታደርገው ሽግግር አንዱ ማሳያ እና ጉልበት ነው።

ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት በምትሰራው ስራ የትራንስፖርት ዘርፉ ጥሩ ሽግግር ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

ባቡርን በታዳሽ ኃይል እንዲሰራ ማድረግ፣ አሮጌ መኪና እንዳይገባ መከልከሉ፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ቁጥር ማስፋት መቻሉ እንዲሁም ጋዝ መመረት መጀመሩ የሽግግሩ ማሳያ መሆናቸውን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያን አረንጓዴ ኢኮኖሚ ስራ በእቅድ እና በውጤት የሚለካ ለማድረግ የ10 ዓመታት የሞተር አልባ ትራንስፖርት ስትራቴጂ ተነድፎ እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የታዳሽ ኃይል ልማትን በማስፋት 500 ሺህ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በፈረንጆች 2030 ስራ ላይ እንዲውሉ ለማድረግ እየተሰራ ስለመሆኑ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ታዳሽ የአውሮፕላን ነዳጅ እንዲኖር እየተሰራ ነው ብለዋል።

በለይኩን ዓለም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.