ለሀገራዊ ምርጫው ስኬታማነት የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል – አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ ሚናውን በአግባቡ ሊወጣ ይገባል አሉ በም/ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የፓርቲው ም/ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ ዋና ጽሕፈት ቤት የስድስት ወራት አፈጻጸም የግምገማ መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡
አቶ አደም ፋራህ በዚህ ወቅት እንዳሉት ፥ መጪው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊና አሳታፊ እንዲሆን ሰላምን ማስጠበቅ፣ ወጣቱ የምርጫ ካርድ እንዲወስድና ድምጽ እንዲሰጥ በትኩረት መስራት ይጠበቃል፡፡
ለዚህም የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ አደረጃጀት በብሄራዊ ትርክት የታነጸ ትውልድ ለመገንባትና የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ ትልቅ ሚና ያለው ስትራቴጂያዊ ኃይል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
መጪው ሀገራዊ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅም የወጣቶች ክንፍ አመራሮችና አባላት የበኩላቸውን ሚና በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ፓርቲው በሁሉም መስክ ባሳካው ውጤታማ አፈጻጸም የወጣቶች ክንፍ የላቀ ሚና እንደነበረው አስታውሰው፥ በቀጣይም ይበልጥ መትጋት እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል፡፡
የብልጽግናን ራዕይ፣ የኢትዮጵያን ሕልም፣ የመደመር እሳቤን፣ ብሔራዊ ትርክትን ማስረጽና ወጣቶችን በማብቃትና በማስተሳሰር ሁለንተናዊ ተሳትፎ እንዲረጋገጥ ማድረግ የክንፉ ዋነኛ አላማ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ብልጽግና ፓርቲ ምርጫው ሰላማዊ፣ ነጻ፣ ገለልተኛ፣ ዴሞክራሲያዊና በሕዝብ ዘንድ ተዓማኒነት ያለው እንዲሆን የያዘውን ግብ ለማሳካት የወጣቶች ክንፍ በአደረጃጀት፣ በሥነ ምግባርና በሀሳብ የበላይነት መስራት ይጠበቅበታል ነው ያሉት፡፡