ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል አደረሳችሁ፣ አደረሰን!!
በክርስቲያኖች ዘንድ ጥምቀት አንድም የመገለጥ፣ ሁለትም የእርቅና ዳግም የመወለድ ምልክት ነው፡፡ በቀደመው ዘመን አዳምና ሔዋን በፈጸሙት ሐጥያት የሰው ልጅ ከአምላኩ ተቀያይሞ የፍዳ ዘመናትን አሳልፏል፡፡ ዳሩ ግን ሰው በሐጥያቱ ልጅነቱን ቢነጠቅም እስከወዲያኛው ጠፍቶ አልቀረም፤ አባቱን ያስከፋ ሥህተት ቢሰራም እስከመጨረሻው ተረግሞ አልኖረም፡፡ አጥቶ የነበረውን የልጅነት ጸጋ በክርስቶስ ዳግም ተቀብሏልና፡፡ ክርስቶስ በፈለገ ዮርዳኖስ የተገኘው እሱ ራሱ ሐጥያት ኖሮበት አይደለም፤ ይልቁንም በሐጥያት እድፍ ለቆሸሸው የሰው ልጅ የእርቅ መንገድ ለመሆን እንጂ፡፡
ሥርዓተ-ጥምቀቱን ስናከብር የጥፋት መፍትሔው ይቅርታ፣ የጸብ መድሃኒቱ እርቅ እንደሆነ እያሰብን መሆን አለበት፡፡ ጸብ አይቀሬ ተፈጥሯዊ ሁነት ነው፡፡ በአባትና በልጅ፣ በፈጣሪና በፍጡር፣ በሕዝብና በሕዝብ መካከል ጸብ ይኖራል፡፡ ነገር ግን ይቅርታና እርቅም አይቀሬ የተፈጥሮ ሁነቶች ናቸው፡፡ ጸብ በአንድ አጋጣሚ የሚከሰት ድንገቴ ክስተት እንደሆነ ሁሉ፥ እርቅ ደግሞ ልዩ ልዩ ሁነቶችን ያቀፈ ጊዜ ወሳጅ ሂደት ነው፡፡ በፈጣሪና በሰው ልጅ መካከል የተፈጠረው የጸብ ግድግዳ መፍረስ የጀመረው በቃል ነው፡፡ አምላክ “ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ” ብሎ ሲናገር የእርቅ ሂደቱም ያኔ ጀምሯል፡፡ የተቋጨው ግን ክርስቶስ በቤተልሄም ተወልዶ፣ በዮርዳኖስ ተጠምቆ፣ መስቀሉን ተሸክሞ ከተሰቀለ በኋላ ነው፡፡
በአምላክና በሰው ልጅ መካከል የተፈጠረው ጸብ በክርስቶስ ፍጻሜውን እንዳገኘ ሁሉ፤ እንደ ሀገር ያሉብንን አለመግባባቶች በጠረጴዛ ዙሪያ ልንፈታቸው፣ የዘመናት የልዩነት እዳዎቻችን ፍጻሜ ሊያገኙ ከጫፍ ደርሰናል፡፡ የሀገራዊ ምክክር ኮምሽኑ ከተቋቋመ ወዲህ ባለፉት ሦስት ዓመታት ሰፊ ቁጥር ያላቸው ዜጎቻችን የተካፈሉበት፣ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፉ እና የልዩነት አጀንዳዎችን ያሰባሰቡ ሰፋፊ መድረኮች ተዘጋጅተዋል፡፡ ተቃርኖዎቻችን በዘላቂነት መፍትሔ የሚያገኙት በምክክራችን ፍጻሜ ነውና እንደሂደቱ ሁሉ ለፍጻሜው ርብርብ እንድናደርግ በዚሁ አጋጣሚ አደራ እላለሁ፡፡
ሥርዓተ-ጥምቀቱ የመገለጥም ምልክት ነው፡፡ ከጥምቀቱ እለት በፊት ክርስቶስ የሚታወቀው በጥቂቶች ብቻ ነበር። በልደቱ የተገለጠውን ብርሃን ለማዳፈን የሞከሩ ሄሮድስን የመሰሉ አካላትም የተሳካላቸው መስሏቸው ነበር። ከሠላሳ ዓመታት በፊት በቤተልሔም የታየው የሰው ልጅ ተስፋ መልሶ የጠፋ መስሎም ነበር። ታይቶ እንደሚጠፋ ኮከብ፤ መጥቶ እንደሚሄድ ዘመን፣ ተከሥቶ እንደሚሠወር መብረቅ የቆጠሩትም ነበሩ።
በጥምቀት ዕለት ግን እውነት ለዓለም ሁሉ ተገለጠች። ከሰማይ እና ከምድር ምስክር መጣ። እንደ ቤተልሔም በጥቂቶች ፊት ብቻ ሳይሆን፣ በዐደባባይ በብዙዎች ፊት ተገለጠ። “እርሱን ስሙት” የሚለው ቃልም ከሰማይ መጣ። ከዚህ በፊት ለእረኞች ብቻ ነበር የተነገረው። ዛሬ ግን ጆሮ ላላቸው ሁሉ ተነገረ። ያኔ በበረት ውስጥ ነበር፤ አሁን ግን በሄኖም ሸለቆ፣ በዮርዳኖስ ወንዝ፣ በዓለም ፊት ሆነ።
ጊዜው ደርሶ የተገለጠ ነገር በዓላማው ፈጻሚዎች እና በዜናው ሰሚዎች መካከል የተለያየ አካሄድ አለው። የዓላማው ፈጻሚዎች ከየት፣ ለምን፣ እንዴት እንደመጣ ያውቃሉ። ወዴት፣ እንዴት እንደሚሄድ ይረዳሉ። ለምን ዓይነት ግብ እንደመጣ ይገነዘባሉ። ስለዚህም ምንም ዓይነት መሥዋዕትነት ለመክፈል ይዘጋጃሉ። አንድ ሆኖ የበራው ሻማ፣ ቀስ እያለ እልፎችን ሲያቀጣጥል ይታያቸዋል። በደመናት ውስጥ የፈነጠቀው ፀሐይ፣ ቀስ እያለ ደመናውን ሲገላልጥ ይታያቸዋል። ከአንድ እንጨት የተለኮሰው እሳት፣ ቀስ እያለ ሲንቦገቦግ ይታያቸዋል።
ዜናውን የሚሰሙት ግን እንደዚያ አይደሉም። ሂደቱን የሚገመግሙት ባገኙት መረጃ መሠረት ብቻ ነው። ዜናው የቀዘቀዘ ሲመስላቸው ጠፍቷል ብለው ያምናሉ። ዜናው የሞቀ መስሎ ሲሰማቸው ደግሞ አለ ብለው ይገምታሉ። የነገሩን መነሻ፣ ሂደትና ግብ በቅርበት አያውቁም። በቤተልሔም የሉም፤ በዮርዳኖስ አልቆሙም። አየን ያሉ ይነግሯቸዋል፤ ሰማን ያሉ ያወሯቸዋል። በዚህም የተነሣ ውሳኔያቸውና ብያኔያቸው በዕለት ክሥተት ላይ የተመሠረተ ነው። ክርስቶስ በሚያስተምርበት ወራት በየተአምራቱ፣ በየክሥተቱና በየኩነቱ ይገኙ እንደነበሩ ሰዎች ዓይነት። በጥብርያዶስ ዳር ሲመግባቸው “እናንግሥህ” ይላሉ፤ በጲላጦስ ዐደባባይ ሲቆም “ስቀለው” ብለው ይፈርዳሉ።
ዛሬ በዚህ የበዓሉ መንፈስ ውስጥ ሆነን የኢትዮጵያን የመገለጥ ጉዞ እንድንመረምር እጋብዛለሁ።
የኢትዮጵያ ዕሴቶች፣ የኢትዮጵያ ሀብቶች፣ የኢትዮጵያ ዐቅሞች፣ የኢትዮጵያ ክንዶች፣ የኢትዮጵያ ውበቶች፣ የኢትዮጵያ ክብሮች፣ የኢትዮጵያ ከፍታዎች – እየተገለጡ ናቸው።
ለውጡ ከመጣ ጀምሮ ላለፉት ጥቂት ዓመታት መሠረቱን ስንሠራ ነበር። የብሉዩን ዘመን ስናድስ፣ የሐዲሱን ዘመን ስንረስስ ነበር። የኦሪቱን ዕዳ ስንደመስስ፣ የሐዲሱን ምንዳ ስናስስ ነበር። የያዘንን ትብታብ ስንበጥስ፣ የለያየንን ግንብ ስናፈርስ ነበር። የፈነጠቀው እስኪፈካ፣ የተወጠነው እስኪሳካ ጠብቀን ነበር። ያልገባቸው እስኪረዱ፣ የገባቸው እስኪራመዱ ዕድል ሰጥተን ነበር።
አሁን ያ ሁሉ አልፎ የኢትዮጵያ የመገለጥ ዘመን መጥቷል። የግብርና ዐቅሟ ተገልጦ ሕዝቦቿን ይመግባል። የማዕድን ዐቅሟ ተገልጦ ዕድገቷን ያፋጥናል። የቱሪዝም ዐቅሟ ተገልጦ ዓለምን ያስደምማል። የቴክኖሎጂ ዐቅሟ ተገልጦ ልማቷን ያቀላጥፋል። የዲፕሎማሲ ዐቅሟ ተገልጦ ተጽዕኖ ፈጣሪነቷን ያጸናል። የአምራችነት ዐቅሟ ተገልጦ የዓለምን ገበያ ይሻማል።
አሁን የኢትዮጵያ ምስክሮች ከላይም ከታችም እየተሰሙ ናቸው። በቤተልሔም ለጥቂቶች ተገልጦ የነበረው የኢትዮጵያ ታላቅነት፣ ዛሬ በዮርዳኖስ ለዓለም ሁሉ እየታየ ነው። ከእንግዲህ የተገለጠችውን ኢትዮጵያን መስማት የግድ ነው። በዮርዳኖስ ስንገለጥ እያዩ በምኩራብ የቀሩት አካላት ብዙ ቢናገሩ አይገርመንም። እኛ የሐዲስ ሰዎች ነን። ብዙ ነገሮችን ቀይረናል፤ አድሰናል። እነርሱ የኦሪት ሰዎች ናቸው። ባልታደሱ ጎዳናዎቻቸው፣ ባረጁ ከተሞቻቸው፣ በደከሙ ቅጥሮቻቸው ውስጥ ይኖራሉ።
ኢትዮጵያ እንደሆነች ከቤተልሔም ወደ ዮርዳኖስ፤ ከዮርዳኖስ ወደ ቆሮንጦስ – ከቆሮንጦስ ወደ ደብረ ታቦር – ከደብረ ታቦር ወደ ቀራንዮ – ከቀራንዮ ወደ ደብረ ዘይት እያለች መጓዟን ትቀጥላለች። ከእንግዲህ እያረገች ትሄዳለች እንጂ ወደ አሮጌ መንደሮቿ አትመለስም። የፈርዖን አስማተኞች የሚፈጥሩት አስማትና መተት ከእንግዲህ አያስፈራትም። ባሕር እንዴት እንደሚከፈል በዮርዳኖስ አይታለችና።
ይህ ዘመን ያለ ጥርጥር የኢትዮጵያ ዘመን ነው። ከኢትዮጵያ እውነት ጋር የሚራመዱ ሁሉ ከኃይል ወደ ኃይል ይራመዳሉ። ይሄን የተረዱ ብዙዎች ከውጭም፣ ከጫካም ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ ነው። ኢትዮጵያም እየተቀበለቻቸው ነው። የቀሩት ብዙዎች ደግሞ የጊዜ ጉዳይ እንጂ እንደሚመጡ እናምናለን። ከጥፋት ልጅ በቀር ማንም ከኢትዮጵያ እውነት አይቀርም።
እምነታችን፣ ሥርዓታችን፣ ባህላችን፣ ቋንቋችን፣ ዜማችን፣ በአጠቃላይ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን በዐደባባይ ለሚገለጥበት የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል በድጋሚ እንኳን አደረሳችሁ።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ጥር 10 ቀን 2018 ዓ.ም