Fana: At a Speed of Life!

በሕብረተሰብ ጤና ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ በሚችሉ የጨው ምርቶች ላይ ርምጃ ተወሰደ

አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሕብረተሰብ ጤና ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ በሚችሉ ከ13 ሺህ ኩንታል በላይ የጨው ምርቶች ላይ ርምጃ ወስጃለሁ አለ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን።

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ነጋሽ ስሜ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፥ ተቋሙ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ጋር በመሆን በምርቶቹ ላይ ሰፊ ክትትል ሲያደርግ ቆይቷል።

ባለስልጣኑ በአዋጅ በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት የተቀነባበሩና በከፊል የተቀነባበሩ ምርቶችን ጥራትና ደኅንነት በምርት ሂደት ላይ ወይም ወደ ገበያ ከተሰራጩ በኋላ ቁጥጥር እንደሚያደርግ አመላክተዋል።

ተቋሙ ባደረገው ክትትልም በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ በሕብረተሰብ ጤና ላይ ጉዳት ሊያስከትል የሚችል ደህንነቱ ያልተጠበቀ ከ13 ሺህ ኩንታል በላይ የጨው ምርት በቁጥጥር ስር መዋሉን ተናግረዋል።

እነዚህ የጨው ምርቶች በሁለት መጋዘኖች ውስጥ ተከማችተው የተገኙ ሲሆን፥ ናሙና በመውሰድ በተደረገ ምርመራ ተገቢውን የጥራት ሂደት ያልተከተሉ መሆናቸው ተረጋግጧል ነው ያሉት።

ማሕበረሰቡን ከምግብ ጋር ከተገናኙ በሽታዎች ለመጠበቅ በምግብ ቁጥጥር ላይ የሚያደርገውን ቁጥጥር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ሕብረተሰቡ ደኅንነታቸው ያልተጠበቁ ምርቶችን ሲመለከት ጥቆማዎችን እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል።

በኃይለማርያም ተገኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.