የኢፌዲሪ አየር ኃይል የኢትዮጵያን ሰላም ለማስጠበቅ በላቀ ዝግጁነት ላይ ይገኛል – ሌ/ጄ ይልማ መርዳሳ
አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢፌዲሪ አየር ኃይል የኢትዮጵያን ሰላም ለማስጠበቅ በላቀ ዝግጁነት ላይ ይገኛል አሉ የአየር ኃይሉ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የኢፌዲሪ አየር ኃይልን 90ኛ ዓመት በማስመልከት የጥቁር አንበሳ የአየር ላይ ትርዒት በቢሾፍቱ እየተካሄደ ነው፡፡
ዋና አዛዡ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የኢትዮጵያ ኩራት የሆነው አየር ኃይሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በላቀ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
አየር ኃይሉ በርካታ ሥራዎችን በመስራት 90 ዓመታትን ያስቆጠረ አንጋፋ ተቋም መሆኑን አውስተው፥ የኢትዮጵያን ሰላም ለማስጠበቅ በላቀ ዝግጁነት ላይ እንደሚገኝ ነው የገለጹት፡፡
የኢትዮጵያን ደህንነት ለማስጠበቅ በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ አቅሙን በየጊዜው እያጠናከረ የሚጠበቅበትን በማድረግ ላይ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
በአየር ትርዒት መርሐ ግብሩ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር እንዲሁም የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች እንዲሁም ሚኒስትሮችን ጨምሮ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ መኮንኖች ተገኝተዋል፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ