የኢትዮጵያ ልጆች በመደመር መተኪያ የሌላት እናት ሀገራችንን ልዕልና ማረጋገጥ አለብን – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ልጆች በመደመር እንደ ትናንት ጀግኖቻችን መተኪያ የሌላት እናት ሀገራችንን ልዕልና ማረጋገጥ አለብን አሉ፡፡
የኢፌዲሪ አየር ኃይልን 90ኛ ዓመት በማስመልከት “የአንበሶቹ ሰማይ ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀው የጥቁር አንበሳ የአየር ላይ ትርዒት በቢሾፍቱ እየተካሄደ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ የወዳጆቻችን የፈቃድ ድጋፍ እንደተጠበቀ ሆኖ የሀገራችንን ጥቅሞችና ፍላጎት ማረጋገጥ በቀዳሚነት የእኛ የኢትዮጵያውያን ግዴታ ነው ብለዋል፡፡
እኛ ያለ ኢትዮጵያ እናት የለንም፥ ኢትዮጵያም ያለ እኛ ልጆች የሏትም በማለት ገልጸው፥ ኢትዮጵያ በተቸገረችበትና በደኸችበት ጊዜ ወደ እንጀራ እናት የሄዱ ወገኖች የእንጀራ እናት ስለማታዛልቅ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
እናት ሀገራችን ልጆቿን ስለማትተው የኢትዮጵያ ልጆች መተኪያ የሌላት ሀገር መሆኗን ተገንዝበን በመደመር እንደ ትናንት ጀግኖቻችን የኢትዮጵያን ጽናትና ልዕልና ማረጋገጥ ከሁላችን ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ