Fana: At a Speed of Life!

አርሰናል ከማንቼስተር ዩናይትድ የሚያደርጉት ፍልሚያ በጉጉት ይጠበቃል

አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 23ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር ዛሬ ቀጥሎ ሲካሄድ የሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል በኢምሬትስ ከማንቼስተር ዩናይትድ ጋር የሚያደርጉት ፍልሚያ በጉጉት ይጠበቃል፡፡

በሊጉ ያለፉትን ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ ያልቻለው የሚኬል አርቴታ ቡድን አርሰናል ወደ አሸናፊነት ለመመለስና መሪነቱን ለማጠናከር ይፋለማል፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት በማይክል ካሪክ እየተመራ በከተማ ተቀናቃኙ ማንቼስተር ሲቲ ላይ ጣፋጭ ድል የተቀዳጀው ተጋጣሚው ማንቼስተር ዩናይትድ በበኩሉ በዛሬው ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡

ሁለቱ ቡድኖች እርስ በርስ ካደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች አርሰናል ሦስቱን በማሸነፍ የበላይነት የያዘ ሲሆን፥ በአንዱ አቻ ተለያይተው በቀሪው አንድ ጨዋታ ደግሞ ማንቼስተር ዩናይትድ ድል ቀንቶታል፡፡

አርሰናልን ከማንቼስተር ዩናይትድ የሚያገናኘው የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ዛሬ ምሽት 1 ሰዓት ከ30 በኢምሬትስ ስታዲየም የሚካሄድ ይሆናል፡፡

የሪካርዶ ካላፊዮሪ እና ፔሮ ሂንካፔ ከጉዳት መመለስን ተከትሎ አርሰናል በውድድር ዓመቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ሙሉ ስብስቡን ማግኘት ሲችል ዩናይትድ በበኩሉ የሞሮኳዊውን የክንፍ ተከላካይ ማዝራዊን ከአፍሪካ ዋንጫ መልስ አገልግሎቱን ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ኒውካስል ዩናይትድ ከአስቶንቪላ፣ ክሪስታል ፓላስ ከቼልሲ እንዲሁም ብሬንትፎርድ ከኖቲንግሃም ፎረስት ቀደም ብሎ አመሻሽ 11 ሰዓት የሚደረጉ የሊጉ ጨዋታዎች ናቸው፡፡

የ23ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብር ሰኞ ምሽት 5 ሰዓት ላይ ኤቨርተን ከሊድስ ዩናይትድ በሚያደርጉት ጨዋታ ይጠናቀቃል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.