Fana: At a Speed of Life!

የአገው ፈረሰኞች በዓልን በድምቀት ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቅቋል

አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 86ኛውን የአገው ፈረሰኞች በዓል ታሪካዊና ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ በድምቀት ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቅቋል አለ የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም መምሪያ፡፡

በመምሪያው የባህል እሴቶች ቡድን መሪና የበዓሉ አስተባባሪ ወለሊ ጌቴ እንዳሉት ÷ የአገው ፈረሰኞች በዓል በጣልያን ወረራ ወቅት ለኢትዮጵያ ነጻነትና ክብር የተዋደቁ ጀግኖች አርበኞችንና ፈረሶቻቸውን ለመዘከር ታስቦ የሚዘጋጅ ነው፡፡

ፈረስ የአገው ሕዝብ የክብሩ መጎናጸፊያና የአክብሮት መገለጫ መሆኑን አውስተው÷ በበዓሉ አከባበር ሥነ ሥርዓት ላይ ማንነት፣ አብሮነት እና ኢትዮጵያዊነትን ከፍ ለማድረግ በትኩረት መሰራቱን ተናግረዋል፡፡

የዘንድሮውን 86ኛው የአገው ፈረሰኞች ማህበር ምስረታ በዓል በድምቀት ለማክበር ኮሚቴ ተዋቅሮ አስፈላጊው ዝግጅት ሲከናወን መቆየቱን አስረድተዋል፡፡

አሁን ላይም በዓሉ ታሪካዊ እና ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ በስኬት እንዲከበር የሚያስችሉ አስፈላጊ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ነው የተናገሩት፡፡

በተለይም ከበዓሉ አከባባር ጋር በተያያዘ የሜዳና የፈረስ ትርዒት ዝግጅት እንዲሁም የባሕል አልባሳት አቅርቦትና ሌሎች ክዋኔዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራቱን አመልክተዋል፡፡

የእንጅባራ ከተማ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በበዓሉ ለሚታደሙ እንግዶች ቀልጣፋና አስተማማኝ መስተንግዶ ለመስጠት ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን አመልክተዋል፡፡

ትራንስፖርትን ጨምሮ ሁሉም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለበዓሉ ታዳሚዎች ምንም አይነት የዋጋ ጭማሪ እንዳያደርጉ አቅጣጫ መቀመጡን አብራርተዋል፡፡

የማህበሩ አባላት በዓሉን በድምቀት ለማክበር ለፈረሶቻቸው አስፈላጊውን እንክብካቤ በማድረግ ልምምድ ማጠናቀቃቸውንም ነው አቶ ወለሊ ያብራሩት፡፡

ነባር የማህበሩ ፈረሰኞች ስልጠና በመስጠት ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቅሰው ÷ ይህም ባህሉን ከትውልድ ትውልድ ለማስተላለፍ ወጣቶች ተሞክሮ እንዲቀስሙ ማስቻሉን አንስተዋል፡፡

በበዓሉ አከባበር ሥነ ሥርዓት ላይ የፈረስ ትርዒት፣ አይሞሎ የፈረስ ጨዋታ፣ ሲምፖዚዬም፣ የባህላዊ ምግብ ዐውደ ርዕይ እና ሌሎች መርሐ ግብሮች እንደሚከናወኑ አስረድተዋል፡፡

የአገው ፈረሰኞች ማህበር ክብረ በዓልን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በ1932 ዓ.ም በውስን ፈረሰኞች የተመሰረተው የአገው ፈረሰኞች ማሕበር አሁን ላይ ከ63 ሺህ በላይ አባላት እንዳሉት ተመላክቷል፡፡

በሀገር ውስጥ እና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች በበዓሉ በመታደም አይረሴ ጊዜን እዲያሳልፉም አስተባባሪው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

86ኛው የአገው ፈረሰኞች በዓል የፊታችን ጥር 23 ቀን 2018 ዓ.ም “የአብሮነት ቅርስ የሰላም ውርስ” በሚል መሪ ሃሳብ እንጅባራ ከተማ በድምቀት ይከበራል።

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.