ለንግድና ኢንቨስትመንት መሳለጥ የመንገድ መሰረት ልማትን ማስፋፋት አስፈላጊ ነው – እንደሻው ጣሰው (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለንግድና ኢንቨስትመንት መሳለጥ የመንገድ መሰረት ልማትን ማስፋፋት አስፈላጊ ነው አሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንደሻው ጣሰው (ዶ/ር)፡፡
በ1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ወጪ የተገነባው የቱሉ ቦሎ – ኬላ 81 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ በዛሬው ዕለት ተመርቋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ርዕሰ መስተዳድር እንደሻው ጣሰው(ዶ/ር)፣ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴዔታ የትም ጌታ አስራት እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
የመንገዱ መጠናቀቅ ለማሕበረሰቡ የመሠረተ ልማት ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት ባለፈ የአዲስ አበባ- ቡታጅራ እንዲሁም አዲስ አበባ- ወልቂጤ- ጅማ ያሉትን አውራ መንገዶች እንደሚያስተሳስር ተመላክቷል፡፡
በተጨማሪም በዜጎች ዘንድ ይፈጠር የነበረን እንግልት በማስቀረት የተቀላጠፈ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችል ተጠቁሟል፡፡
እንደሻው ጣሰው(ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ መንገዱ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማሳለጥ እንዲሁም ባለሃብቶች በአካባቢው መዋዕለ ንዋያቸው እንዲያፈሱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡
በሕዝቦች መካከል ያለው የንግድ፣ ባህል እና የአኗኗር መስተጋብር ይበልጥ እንዲጠናከ ሚናው ጉልህ መሆኑንም ነው ያወሱት፡፡
አቶ የትም ጌታ አስራት በበኩላቸው መንግሥት መሠረተ ልማት የስልጣኔና የለውጥ ቁልፍ መሳሪያ መሆኑን በመገንዝብ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡
በሰማኸኝ ንጋቱ