Fana: At a Speed of Life!

የአነስተኛ አውሮፕላን ማረፊያዎች መስፋፋት ለቱሪዝምና ኢንቨስትመንት መነቃቃት…

አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አነስተኛ የአውሮፕላን ማረፊያዎችን በተለያዩ አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው አለ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን፡፡

በባለሥልጣኑ የኤሮድሮም ሴፍቲና ስታንዳርድ ዳይሬክተር ምስራቅ ጥላሁን ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ተደራሽነትን ይበልጥ ለማስፋፋት በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡

ለዚህም የተለያየ ደረጃ ያላቸው አውሮፕላን ማረፊያዎችን በተለያዩ አካባቢዎች መገንባትና ወደ ሥራ ማስገባት ላይ ትኩረት መደረጉን አመልክተዋል፡፡

አሁን ላይ በተለያዩ አካባቢዎች እየተገነቡ ከሚገኙት አውሮፕላን ማረፊያዎች በተጨማሪ አነስተኛ አውሮፕላን ማረፊያዎች እየተገነቡ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

በአነስተኛ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ላይም የክልል መንግሥታት፣ ከተማ አስተዳደሮች፣ ባለሃብቶች እና የግል ድርጅቶች እንዲሳተፉ መደረጉን ነው የገለጹት፡፡

ይህን ተከትሎ እስካሁን አነስተኛ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ለማከናወን ከተለያዩ አካላት 46 ጥያቄዎች መቅረባቸውን አብራርተዋል፡፡

ከእነዚህ ውስጥም ሰባት የሚሆኑት ወደ ግንባታ ሥራ መግባታቸውን ጠቁመው÷ ሁለቱ ደግሞ ግንባታ አጠናቅቀው ኦፕሬሽን መጀመራቸውን አስረድተዋል፡፡

ሌሎችም ግንባታ መጀመር የሚያስችሉ የተለያዩ ሒደቶችን በማከናወን ላይ እንደሚገኙ ዳይሬክተሯ ጠቅሰዋል።

ቦታ መረጣ እና የተለያዩ ቴክኒካል ድጋፎች ከማድረግ ጀምሮ የኢትዮጵያ አቪዬሽን ባለስልጣን አስፈላጊውን ትብብር እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አነስተኛ የአውሮፕላን ማረፊያዎችን ማስፋፋት የቱሪዝም ተደራሽነትን ለማጠናከር፣ ኢንቨስትመንትን ለማሳለጥና የአካባቢዎችን ዕምቅ ሃብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም አስገንዝበዋል፡፡

ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ በአነስተኛ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታና በትራንስፖርት ዘርፍ የግል ባለሃብቶችን ማሳተፍ የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ መደረጉ ይታወሳል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.