ኢትዮ ቴሌኮም በገጠር የሞባይል ኔትዎርክ ትስስርን ለማጠናከር…
አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በገጠር አካባቢዎች የሞባይል ዳታ እና የድምጽ ጥሪ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማጠናከር እየተሰራ ነው አሉ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ፡፡
ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ እንዳሉት÷ የገጠር አካባቢዎችን የዲጂታል መካተት ለማረጋገጥ እና የገጠር ነዋሪዎችን ከዲጂታሉ ዓለም ጋር ለማቀላቀል ሰፊ የማስፋፊያ ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡
ለዚህም የገጠር ሞባይል ጣቢያዎችን ማጠናከር ላይ ትኩረት መደረጉን ጠቁመው÷ ባለፉት 6 ወራት ብቻ በ102 ወረዳዎች ውስጥ 130 የገጠር ሞባይል ጣቢያዎች መገንባታቸውን ተናግረዋል፡፡
ይህን ተከትሎም በ332 ቀበሌዎችና መንደሮች ቴሌኮምን ተደረሽ በማድረግ ከ761 ሺህ በላይ ዜጎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
ጣቢያዎቹ የተገነቡባቸው አካባቢዎች በአማካይ ከከተሞች በ23 ነጥብ 76 ኪ.ሜ እንዲሁም ከሌሎች የሞባይል ጣቢያዎች በ18 ነጥብ 77 ኪ.ሜ ርቀት ላይ እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ከማድረግ አንጻር ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል፡፡
በተለይም ስማርት ሲቲ፣ ስማርት ካምፓስ፣ የመንግሥት አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ ማድረግ እና የፋይዳ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያን የመሳሰሉ ፕሮጀክቶችን ለተለያዩ የክልል እና የፌዴራል ተቋማት እያቀረበ ይገኛል ብለዋል፡፡
በዚህም በግማሽ ዓመቱ በኢንተርፕራይዝ ሶልዩሽን ዘርፍ 3 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ገቢ በማመንጨት 48 ነጥብ 5 በመቶ አፈጻጸም ማስመዝገቡን ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል በመንፈቅ ዓመቱ 112 ተጨማሪ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት የተገነቡ ሲሆን÷ በአጠቃላይ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት ብዛትን 1 ሺህ 150 መድረሱን ጠቅሰዋል፡፡
ማዕከላቱ የተከፈቱት ከዚህ በፊት ምንም አይነት የአገልግሎት መስጫ ማዕከል ያልነበራቸው ከተሞች ላይ እና ከፍተኛ የተጠቃሚ ፍሰት ባለባቸው አካባቢዎች መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ይህም ለደንበኞች ይበልጥ ተደራሽ መሆን ከማስቻሉም በላይ በውድድር ገበያው ላይ በሁሉም ቦታዎች በቅርበት በመገኘት ተመራጭ የሽያጭ ቻናል መፍጠር ያስችላል ነው ያሉት፡፡
በመላኩ ገድፍ