በነዳጅ ቅሸባ በዓመት ከ5 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ይመዘበራል
አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ሕገ ወጥ የነዳጅ ግብይትን ለመቆጣጠር ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል አሉ።
የነዳጅ አቅርቦት፣ ሥርጭት እና ግብይት ላይ ያተኮረ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ኮንፈረንስ ተካሂዷል።
ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት፥ ነዳጅ ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች፣ የሀገርን ደህንነት ለማስጠበቅና ለሁለንተናዊ ዕድገት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።
ለዚህም መንግሥት በዓመት እስከ 700 ቢሊየን ብር በመመደብ የነዳጅ ግዥ እያከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በዘርፉ የሚስተዋለውን ስብራት ለመጠገን በርካታ የማሻሻያ ርምጃዎች መወሰዳቸውን ገልጸው፥ ለአብነትም አዲስ የጂፒኤስ ቴክኖሎጂ በመተግበር የነዳጅ ሥርጭትን መቆጣጠር መቻሉን ጠቅሰዋል።
በዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ ካሉት 5 ሺህ 400 አውቶ ቦቴዎች ውስጥ 4 ሺህ 751 አውቶ ቦቴዎች ሲስተም ላይ ተጭነው ቁጥጥር እየተደረገባቸው ነው ብለዋል።
ይሁን እንጂ ለሕዝብ ጥቅምና ለኢኮኖሚ ዕድገት የታለመውን ነዳጅ በስግብግብነት ለግል ጥቅማቸው ለማዋል በተለያዩ አካባቢዎች ሰው ሰራሽ እጥረትን እየፈጠሩ መሆኑን አንስተዋል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ደስታው መኳንንት (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ሕገ ወጥ የነዳጅ ግብይት የሀገርን ኢኮኖሚ ከመፈተን ባለፈ ዜጎችን ለእንግልት እየዳረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ከጅቡቲ ነዳጅን በጊዜ ጭነው ለገበያ ከማቅረብ ፋንታ ረጅም ጊዜ ድንበር ላይ እና መንገድ ላይ እንዲቆይ ማድረግ፣ ከመዳረሻ ውጭ ሌላ ቦታ ለማራገፍ መሻት፣ ማደያ ላይ ነዳጅ እያለ የለም ማለት፣ ነዳጅን ከተመን ውጪ መሸጥና የአውቶቦቴዎችን የጉዞ ታሪክ ማጥፋት በዘርፉ የሚስተዋሉ ዋና ዋና ተግዳሮቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በአማካይ ከአንድ ነዳጅ መጫኛ ቦቴ 500 ሊትር እንደሚቀሸብ ገልጸው፥ በዚህም በዓመት ከ5 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ይመዘበራል ብለዋል።
አብዛኛዎቹ የነዳጅ ማደያዎች ሲገነቡ በሕጋዊ መንገድ ለመሥራት ሳይሆን ሕገወጥ ንግድን የማሳለጥ እሳቤን አልመው እንደሆነ በተደረገ ጥናት መረጋገጡን አስረድተዋል።
የነዳጅ አቅርቦትን ከፍላጎት ጋር ለማጣጣምና እና ፍትሃዊ የነዳጅ ሥርጭትን ለማሳለጥ በትኩረት እንደሚሰራም ዋና ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል።
በመላኩ ገድፍ