Fana: At a Speed of Life!

16 የፀሐይ ኃይል ልማት ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው አገልግሎት ይጀምራሉ

አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር 16 የፀሐይ ኃይል ልማት ፕሮጀክቶች በቅርቡ ተጠናቅቀው አገልግሎት ይጀምራሉ አለ።

በሲዳማ ክልል ማዕከላዊ ሲዳማ ዞን የሎካ አባያ ወረዳ የመሬራ ከተማ ከፀሐይ ብርሃን የሚመነጭ 633 ኪሎ ዋት ኃይል ተጠቃሚ መሆኗ ይፋ ተደርጓል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ በብሔራዊ የኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር የራቁ አካባቢዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የአደሌ ፕሮጀክት እየተተገበረ ነው።

የመሬራ የኃይል ማመንጫ የፕሮጀክቱ አካል መሆኑን ገልጸው፤ ፕሮጀክቱ ከዓለም ባንክ በተገኘ 400 ሚሊየን ብር ብድር እውን መሆኑን ተናግረዋል።

ይህንን ፕሮጀክት ጨምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ 22 ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው አገልግሎት እየሰጡ እንደሆነ ገልጸው፤ 16 ተጨማሪ የፀሐይ ኃይል ልማት ፕሮጀክቶች በቅርቡ ተጠናቅቀው አገልግሎት ይጀምራሉ ብለዋል።

በ2022 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ አካባቢዎችን 75 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በኦፍ ግሪድ ቴክኖሎጂ በተለይም በፀሐይ ኃይል ልማት ዘርፍ ከ26 በመቶ በላይ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

የሲዳማ ክልል ውሃ፣ ኢነርጂ እና ማዕድን ቢሮ ኃላፊ ከበደ ጋኖሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የመሬራ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ለአካባቢው ማህበረሰብ የረጅም ጊዜ ጥያቄ ምላሽ የሰጠ እንደሆነ ተናግረዋል።

በክልሉ የንጹህና ታዳሽ ኃይል ተጠቃሚነት ሽፋንን ለማሳደግ ከ12 ሺህ 500 በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ አምስት ፕሮጀክቶች እየተከወኑ ይገኛሉ ነው ያሉት።

በጎህ ንጉሱ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.