Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በብልጽግና ጎዳና እየገሰገሰች ለመሆኗ ምስክር የሆነው የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት…

አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ኢትዮጵያ በብልጽግና ጎዳና በፍጥነት እየገሰገሰች መሆኗን ለተመልካች የሚያሳይ፣ ለሰሚ የሚናገር፣ ያላመነን የሚከራከር፣ የተጠራጠረን የሚያጸና ቋሚ ምስክር ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት በአማራ ክልል ከጎርጎራ በመቀጠል የ’ገበታ’ ውጥን ሁለተኛ ፕሮጀክት የሆነውን ሎጎ ሐይቅ ሪዞርት መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት÷ ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ በብልጽግና ጎዳና በፍጥነት እየገሰገሰች ለመሆኗ ምስክር ነው ብለዋል።

የመንግሥት ግብ አንዲት ጠንካራ፣ የበለጸገች፣ የታፈረች፣ የተከበረች፣ ፍትሃዊት፣ ዴሞክራሲያዊት እና ሕብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን መገንባት እና ማጽናት ነው በማለት ገልጸው÷ የሎጎ ሐይቅ ፕሮጀክት ይህንን የሚያሳይ ህያው ምስክር መሆኑን ተናግረዋል።

የመደመር መንግሥት ግቡ ሀገረ መንግሥት መገንባት ነው፤ የማይሰራውን ቃል አይገባም ቃል የገባውንም አይዘነጋም ብለዋል።

ሐይቅ ከሎጁ በፊት እና በኋላ የነበረው ገጽታ የተለየ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ለዚህም ለውጥ የአመራር ቁርጠኝነት መነሻ እንደሆነ አመልክተዋል።

የሪዞርቱ ህንጻ ከ130 ሜትር በላይ ርዝመት ያለው፣ 350 ሰው በላይ መያዝ የሚችል ሁለገብ አዳራሽ የያዘ፣ 3 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የአስፋልት መንገድ፣‎ በ67 ክፍሎች 80 አልጋዎች፣ ሙሉ ስፓ፣ ‎የመዋኛ ገንዳዎች፣ ‎የውስጥና የውጭ የስፖርት ማዘውተሪያ፣‎ የአትክልትና ፍራፍሬ ስፍራዎች፣ በአንዴ ከ100 በላይ መኪናዎችን መያዝ የሚያስችል የመኪና ማቆሚያ እና ‎የሔሊኮፕተር ማረፊያ ስፍራ ማካተቱንም አብራርተዋል።

ፕሮጀክቱ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ በቀጥታ በአማካኝ ከ1 ሺህ በላይ ሰራተኞችን አሳትፏልም ነው ያሉት።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ በላይነህ ክንዴ የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ፕሮጀክትን ከማሳካት ባሻገር በሐይቅ ከተማ የሚገኘውን አንደኛ እና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመገንባት፣ ኮምፒዩተር እና መጻሕፍት አሟልቶ ማስረከቡን በመግለጽ÷ ለተግባራቸውም አመስግነዋል።

ፕሮጀክቱ አንድም ቀን በምንም አይነት ሁኔታ ሳይቋረጥ መሰራቱን ጠቅሰው÷ ለዚህም ለአካባቢው ህዝብ ምስጋና አቅርበዋል።

በሶስና አለማየሁ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.