Fana: At a Speed of Life!

በአዋሽ ባንክ የዲጂታል ክፍያ ስርዓት የ1 ትሪሊየን ብር ክፍያ ተከናወነ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት 6 ወራት በአዋሽ ባንክ የዲጂታል ክፍያ ስርዓት የተከናወነው የክፍያ መጠን አንድ ትሪሊየን ብር ደረሰ።

ባንኩ ከዛሬ ጀምሮ “ለላቀ የደንበኞች እርካታ እንተጋለን” በሚል መሪ ሐሳብ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ የደንበኞች ሳምንት ያካሂዳል።

የአዋሽ ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ ፀሐይ ሽፈራው ባንኩ ከደንበኞች ጋር ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ 1 ሺህ ቅርንጫፎች እንዲሁም 24 ሰዓት አገልግሎት በሚሰጡ የዲጂታል ባንኪንግ ለደንበኞቹ አገልግሎቶች እየሰጠ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ባንኩ ስራ ፈጣሪዎችና አምራቾች ሀሳባቸውን ወደ ቢዝነስ እንዲቀይሩ በማስቻል ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገቡንም አውስተዋል።

የደንበኞች ሳምንት መርሐ ግብሩ ደንበኞችን ለማመስገን እና እውቅና ለመስጠት፣ የባንኩን ሰራተኞች ለተሻለ ስራ ለማነሳሳት እንዲሁም የደንበኞችን አስተያየት በመቀበል ለበለጠ ለውጥ ለመስራት ያለመ ነው ተብሏል።

ደንበኞች በአቅራቢያቸው የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ቅርንጫፎችን እያስፋፋ እና የዲጂታል ባንኪንግ ስርዓትን በበለጠ ለማዘመን እየሰራ እንደሚገኝም ተመላክቷል።

በሔኖክ ለሜ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.