በአፍሪካና በአውሮፓ መካከል ያለው አጋርነት በጋራ መበልጸግ ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፍሪካ እና በአውሮፓ መካከል ያለው አጋርነት በጋራ መበልጸግ ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ2ኛው የጣሊያን-አፍሪካ ጉባዔ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በትብብር አዲስ የአፍሪካ አውሮፓ ግንኙነትን መቅረጽ እንደሚቻል ገልጸዋል።
ትብብሩ በጥገኝነት ሳይሆን በመከባበር እንዲሁም በጋራ መበልጸግ ላይ የተመሰረተ ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የጣሊያን “ማቲ ዕቅድ” በኢነርጂ ደህንነት፣ በዘላቂ ልማት፣ በስደት አስተዳደር እና በሰው ሀብት ልማት ላይ በአጋርነት እና በጋራ ጥቅም ላይ እንደሚያተኩር ተናግረዋል።
የዚህ ራዕይ አካል የሆነችው ኢትዮጵያ ከቃላት ወደ ተግባር ለመሸጋገር ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ አፍሪካን ከዓለም ጋር በማገናኘት ረገድ በርካታ ስራዎችን እየሰራች መሆኑን አንስተው፤ በአቪዬሽን፣ በሎጂስቲክስ እና ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን በማዘጋጀት የአህጉሪቱ ድምጽ እንዲሰማ እየሰራች ነው ብለዋል።
የአፍሪካ ትልቁ ጥንካሬ የሆነው ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል በዲጂታል ቴክኖሎጂ እና በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፎች እንዲሰማራ ኢንቨስትመንት በማድረግ ለስራ ዕድል ፈጠራ እና የወደፊት ተግዳሮቶችን ለመፍታት ቁልፍ እንደሆነ ጠቁመዋል።
የማቲ ዕቅድ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ኢትዮጵያ እየተገበረችው ካለው የታዳሽ ኃይል፣ የአየር ንብረት፣ የስማርት ግብርና፣ መሠረተ ልማት፣ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና የሰው ኃብት ካፒታል ልማት ጋር የተጣጣመ መሆኑን አመልክተዋል።
በአፍሪካ እና በአውሮፓ መካከል ያለው አጋርነት የጋራ ብልጽግናን ሊያመጣ እንደሚችል አንስተው፤ በጣሊያን እና በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር ኢትዮጵያ ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
በዮናስ ጌትነት