Fana: At a Speed of Life!

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በነገው ዕለት የሚጀመረውን የዓቢይ ጾም ሱባኤ በማስመልከት አባታዊ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም በነገው ዕለት የሚጀመረውን የ2018 ዓ.ም የጌታችን የአምላካችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የዓቢይ ጾም ሱባኤ በማስመልከት አባታዊ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም ጾም መጾም ከፍቅረ መባልዕት፣ ከፍቅረ ንዋይና ከፍቅረ ሢመት ፍላጎት ጨርሶ መራቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የጾም ዋና ዓላማ ሥጋዊ ፍላጎትን መግራት፣ በምትኩ ደግሞ መንፈሳዊ ፍላጎትን ማጎልበት እንደሆነ ተነግሮናል ያሉት ቅዱስነታቸው÷ በመሆኑም ይህንን መርሕ ጠብቀን መጾም ግዴታችን ይሆናል ብለዋል።

የጾሙ ዓላማውና ግቡ ጽኑዕ ሃይማኖትን፣ እውነተኛ ፍቅርን፣ ዘላቂ ሰላምን፣ ልባዊ አንድነትን፣ የማይናወጽ ፍትሕንና እኩልነትን፣ ወሰን የሌለው ርኅራሄን በውስጣችን ብሎም በዓለማችን ማሥረጽ እንደሆነ በውል ተገንዝበን ጾሙን መጾም ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።

በጾሙ ወቅት ከልብ በመጸለይ፣ የተራቡትን በማጉረስ፣ የታረዙትን በማልበስ፣ የተጠሙትን በማጠጣት፣ የተጣሉትን በማስታረቅ፣ ፍትሕ ለተነፈጉትም እውነተኛ ፍትሕን በመስጠት፣ ጾሙን መጾም እንደሚገባ አባታዊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.