የመዲናችን አስደናቂ ለውጥ ለጉባዔዎቹ ትልቅ ሞገስ ሆኗል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የኢትዮጵያዊያን እንግዳ ተቀባይነትና የመዲናችን አስደናቂ ለውጥ ለጉባዔዎቹ ትልቅ ሞገስ ሆኗል አሉ።
ከንቲባዋ መዲናዋ ያስተናገደቻቸው 39ኛው የአፍሪካ ህብረት እና 2ኛው የጣሊያን-አፍሪካ ጉባዔዎች በስኬት እንዲጠናቀቁ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
ጉባዔዎቹ ከወትሮው በተለየ መልኩ በታላቅ ድምቀትና ስኬት ተጠናቅቀዋል ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ ጉባዔዎቹ በውቧ መዲናችን አዲስ አበባ ፍጹም ስኬታማ በሆነ መንገድ ተካሂደዋል ብለዋል።
ለዚህም የኢትዮጵያዊያን ለዘመናት የዘለቀ እንግዳ ተቀባይነት እንዲሁም የመዲናችንን አስደናቂ ለውጥ ለጉባዔዎቹ ትልቅ ሞገስ ሆኗል ነው ያሉት።
የከተማዋ ነዋሪዎች ላሳዩት እንግዳ አክባሪነት፣ ትዕግስትና አጋርነት እንዲሁም የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለሰጡት ጥራት ያለው እና ቀልጣፋ አገልግሎት ምስጋና አቅርበዋል።
ከተማችንን ሁሌም አዲስ ገፅታ እና መንፈስ በማላበስ ይህ ጉባኤ እንዲሳካ ላደረጋችሁ የከተማችን አመራሮች እና ሰራተኞች እንዲሁም ከነዋሪው ጋር በመቀናጀት በቁርጠኝነት ለሠራችሁ የጸጥታ አካላት በራሴና በከተማ አስተዳደሩ ስም ላቅ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለሁ ብለዋል።
በተለይም ደግሞ ከካዛንቺስ እስከ ቦሌ ብራስ ያላችሁ የግል ተቋማትና ግለሰቦች ለሌት ተቀን ትጋታችሁና ቀና ትብብራችሁ ምስጋና ይገባችኋል ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።