የረመዳን ወር በመረዳዳትና በመተሳሰብ ልናሳልፈው ይገባል – ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ታላቁን የረመዳን ወር በመረዳዳትና በመተሳሰብ ልናሳልፈው ይገባል አሉ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ።
የረመዳን ወርን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት ፕሬዚዳንቱ÷ ለመላው ሙስሊም ማሕበረሰብ እንኳን ለ1447ኛው የረመዳን ወር በሰላም አደረሳችሁ በማለት የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ረመዳን ከአምስቱ የእስልምና ማዕዘናት አንዱ በመሆኑ ሁሉም ሕዝበ ሙስሊም እንዲፆም በአላህ የታዘዘ ወር ነው ብለዋል።
ረመዳን የአንድነትና የመተሳሰብ ወር መሆኑን ገልጸው÷ የይቅርታ፣ የእዝነት እና የማህበራዊ ትስስር ጊዜ በመሆኑ ሁሉም የእምነቱ ተከታዮች ከበጎ ስራዎች ጋር እንዲገናኙ አስገንዝበዋል።
አቅመ ደካሞችን በመርዳት፣ ማዕድን በማካፈል፣ በመተሳሰብና አላህን በመለመን ወሩን ማሳለፍ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ረመዳን የሰላም ወር በመሆኑ ሁሉም ከግጭት እና ከፀብ በመራቅ እንዲያሳልፍ ገልጸው÷ መንፈሳዊ ልዕልና የሚኖረው ሰላም ሲኖር በመሆኑ ለሀገራችን ሰላም እና ለሕዝባችን ደኅንነት ዱዐ ልናደርግ ይገባል ብለዋል።
የረመዳን ጾም ጨረቃ በሒጅራ አቆጣጠር ሻዕባን 29 ማክሰኞ ቀን ከታየች ረቡዕ ካልታየች ደግሞ ሐሙስ የካቲት 12 ቀን 2018 ዓ.ም ይሆናል፡፡
በሰአዳ ጌታቸው