አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም የሁሉንም አካላት ተሳትፎ ይፈልጋል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ሰላምን አስተማማኝ እና ዘላቂ ለማድረግ የሁሉም አካላት ተሳትፎ ያስፈልጋል አሉ፡፡
8ኛው ሀገር አቀፍ የሰላም እና ፀጥታ የጋራ ምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በተለያየ ወቅት የተከሰተ ግጭት ትውልዱን ዋጋ እያስከፈለ ያለ እዳ ነው ብለዋል።
ይህ ግጭት ወደ ቀጣይ ትውልድ እንዳይተላለፍ ዛሬ ላይ እጅ ለእጅ ተያይዞ በመስራት ህዝቡን በማሳተፍ አስተማማኝ እና ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
ነገን ዛሬ ለመገንባት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከር ማህበራዊ ትስስርን ማጎልበት ለዘላቂ ሰላም መስፈን ትልቅ ሚና አለው ብለዋል።
ከዚህ አንጻር በመዲናዋ አረአያነት ያለው ተግባር እየተከናወነ እንደሆነ ገልጸው፤ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የማጠናከር ተግባር በየትኛውም አካባቢዎች መተግባር እንደሚገባው ጠቁመዋል።
መንግሥት ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ የገለጹት የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ በበኩላቸው፤ በተለያዩ አካባቢዎች የህዝብን ሰላም የሚያውኩ አካላት ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።
በተለይም ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን በጠመንጃ አፈሙዝ ለማስመለስ የሚደረገው ጥረት ጊዜው ያለፈበት መሆኑን ጠቅሰው፤ ለሰላማዊ አማራጭ ቅድሚያ በመስጠት በትብብር መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
ዘንድሮ የሚደረገው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም በመድረኩ ጥሪ ቀርቧል።
በሚልኪያስ አዱኛ