Fana: At a Speed of Life!

ዓድዋ በኅብረት የተሰለፉ ጀግኖች ድል የነሱበት የጽኑ መንፈስና የከፍታችን ተምሳሌት ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ለ130ኛው የዐድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው÷ የዓድዋ ድል የጥቁር ሕዝቦች የድል አክሊል፤ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን ትተው፣ በአንድነት የተሰለፉበትና ድል ያደረጉበት የወል እውነት፣ የወል ክብር፣ የወል ታሪካችን ነው ብለዋል።

ዓድዋ በመልካምነት የተባበሩ ልቦች፣ በፍቅር ጉልበት የበረቱ ክንዶች፣ በኅብረት የተሰለፉ ጀግኖች ድል ያስመዘገቡበት የጽኑ መንፈስና የከፍታችን ተምሳሌት እንደሆነም አውስተዋል፡፡

ከዓድዋ የምንማረው ታላቅ እውነትና የወል ውርስ አንድ ስንሆን ማሸነፍ እንደምንችል ነው ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በዚህ በማይደበዝዝ ዘለዓለማዊ የድል ማኅተም፣ ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን ሀገርን ከነሙሉ ክብሯ ለኛ ዘመን አሸጋግረዋል ነው ያሉት።

በደም በጻፉት ደማቅ የታሪክ ድርሳን ለሀገር ፍቅርና ክብር መሥዋዕት መሆን ምን ማለት እንደሆነም በተግባር አስተምረውናል ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን፡፡

ሀገራችን በልጆቿ ጠንካራ አንድነት አያሌ ፈተናዎችን ተሻግራለች፤ በኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን ስንቆም ዓለምን ያስደመሙ ድሎችን መፈጸም እንደምንችልም በተደጋጋሚ አሳይተናል ብለዋል።

ዛሬም ጠንካራና የታፈረች ኢትዮጵያን ለመገንባት በጋራ ጉዳዮች ላይ መግባባትና ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ ገንቢ ሚናችንን መወጣት ይገባናል ሲሉ አስገንዝበዋል።

በሁሉም ብሔሮች ብሔረሰቦች ውስጥ ያሉ እምቅ ጥበቦች፣ ዕውቀቶችና እሴቶችን በመቀመር ለሀገር የከፍታ ጉዞ መጠቀም እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

በወል ጉዳዮች መግባባት ስንፈጥር የሚኖረን የተደመረ ዐቅም፣ ከልዩነት ፖለቲካ ወደ አንድነት፣ ከድህነት ወደ ብልጽግና የምናደርገውን ጉዞ እንደሚያፋጥነው አስረድተዋል፡፡

ዓድዋ የድል አክሊላችን ነው ስንል፣ ያለፈውን ውድ ታሪካችንን ከዛሬና ከነገ የምንገምድበት ክር፣ በሁሉም መስክ የታፈረችና የኮራች ሀገርን የምንገነባበት ጽኑ መሠረት ስለሆነም ጭምር ነው ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.