Fana: At a Speed of Life!

በከተሞች ዕድገት ላይ ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ ያለው የኮሪደር ልማት…

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሲዳማ ክልል የተሰሩ የኮሪደር ልማት ስራዎች በከተሞች ዕድገት ላይ ተጨባጭ ውጤት አስመዝግቧል አለ የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ፡፡

የቢሮው ኃላፊ አቶ ወሰንየለህ ስምኦን ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በኮሪደር ልማት በተሰሩ በርካታ ስራዎች ከተሞችን ጽዱና ለኑሮ ምቹ ማድረግ ተችሏል፡፡

በክልሉ ከሚገኙ ከተሞች መካከል ሀዋሳ ላይ የኮሪደር ልማት ስራው በሁለት ዙር መከናወኑን ጠቅሰው÷ ከተማዋን የሚመጥን፣ ለነዋሪዎች ምቹ እና የንግድ እንቅስቃሴን የሚያሳልጥ ስራ መሰራቱን አመልክተዋል፡፡

በከተማው የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቁመው÷ በሀዋሳ ሀይቅ ዙሪያ ተጨማሪ መሰረተ ልማቶችን ለመስራት አንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በክልሉ ወንዶገነት፣ ይርጋለም፣ አለታ ወንዶ፣ በንሳ ዳዬ፣ ይርባ ቦርቻ፣ ለኩ እና አለታ ጩኮ ከተሞች ላይ የኮሪደር ልማት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

የኮሪደር ልማት ስራው የተሽከርካሪዎች መንገድ፣ ምቹ የእግረኞች መንገድ፣ የብስክሌት መንገድ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ፣ የሕጻናት መጫወቻ እና የመዝናኛ ስፍራዎችን ያካተተ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የኮሪደር ልማት እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎች በጥራት እና በስፋት መከናወናቸው የቱሪዝም እንቅስቃሴውን እያሳደገ እንደሚገኝ ገልጸው÷ ለበርካቶች የስራ ዕድል መፍጠሩንም ተናግረዋል፡፡

የከተሞች ዕድገት እየጨመረ መሆኑን ጠቁመው÷ በሁሉም የክልሉ ከተሞች ዘላቂ መሰረት ልማት የማሟላት ስራ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ከተሞችን ለኑሮ ምቹ፣ ጽዱ እና የገቢ ምንጭ ከማድረግ አንጻር የኮሪደር ልማት ስራዎች ተጨባጭ ለውጥ ማምጣታቸውንም አስረድተዋል፡፡

የተጀመረው የስማርት ከተማ ግንባታ በኮሪደር ልማት እየተፋጠነ መሆኑን አንስተው÷ በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ከተሞች ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.