Fana: At a Speed of Life!

ለሕዝብ መዝናኛ የተዘጋጀን ይዞታ ላልተገባ አካል በሙስና ሰጥተዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች ተከሰሱ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለሕዝብ መዝናኛ የተዘጋጀን ይዞታ ላልተገባ አካል በሙስና ሰጥተዋል የተባሉ አመራሮችን ጨምሮ 30 ተጠርጣሪዎች ተከሰሱ።

ክሱ የተመሰረተው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ የወንጀል ሕጉንና የሙስና አዋጁን ጠቅሶ በግለሰቦቹ ላይ በየተሳትፎ ደረጃቸው ዝርዝር ክስ አቅርቦባቸዋል።

ክስ ከቀረበባቸው ተከሳሾች መካከል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ የቀድሞ ም/ኃላፊ ሞሊቶ አባይነህ፣ በቢሮው ቅሬታ አቤቱታ ባለሙያ የነበሩት ግርማ ተፈራ፣ የቢሮው የመልሶ መልማት ዳይሬክተር የነበሩት ግዛቸው ሙሉጌታ፣ የቢሮው ቢሮ የቅሬታ እና አቤቱታ ባለሙያ የነበሩት አድማሱ አድነው፣ የቢሮው ካርታ ዝግጅት ባለሙያ የነበሩት ሰለሞን በላይ፣ የአዲስ አበበ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ ዐቃቢ ሕግ የነበሩት አብዮት ጁፋራ እና የቦሌ ክ/ከተማ መሬት ልማትና አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ የነበሩት ቸርነት አበበ ይገኙበታል፡፡

በዚህም በቀረበው ክስ ላይ እንደተመላከተው፤ ከ2012 ዓ.ም እስከ 2016 ዓ.ም በተለያዩ ቀናትና ወራት ከ1ኛ እስከ 5ኛ ያሉት ተከሳሾች በአዲስ አበበ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ውስጥ አመራርና ባለሙያ ሆነው ሲሰሩ እንደነበር ተመላክቷል፡፡

6ኛ ተከሳሽ የከተማው ፍትህ ቢሮ ውስጥ ዐቃቤ ሕግ፣ ከ7ኛ እስከ 15ኛ ተራ ቁጥር ላይ የተጠቀሱት ተከሳሾች ደግሞ በቦሌ ክ/ከ እና በክ/ከተማው ወረዳ 13 ውስጥ በተለያዩ ደረጃዎች ተመድበው በሚሰሩበት ጊዜ ከ16ኛ እስከ 19ኛ ተራ ቁጥር ላይ ከተጠቀሱት ተከሳሾች ጋር በጥቅም መተሳሰራቸው በክሱ ተጠቅሷል።

በዚህም ከ1ኛ እስከ 15ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱት ተከሳሾች እርስ በርሳቸው በመናበብ ከ16ኛ እስከ 19ኛ ተራ ቁጥር ከተገለፁት ተከሳሾች ጋር በጥቅም በመመሳጠር በወረዳ 13 ክልል ውስጥ ታቦት ማደሪያ ፊት ለፊት ያለን መሬት ባንክ ቋት ውስጥ የሚገኝ እና በወረዳ ደንብ ማስከበር ጽ/ቤት ጥበቃ እንዲደረግለት በከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ መጽደቁ ተጠቁሟል፡፡

ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ በዓድዋ ፓርክነት የሚታወቅና በከተማ ደረጃ መናፈሻነት ተይዞ የነበረውን ከ1ዐኛ መዋቅራዊ ፕላን ከ2010 ዓ.ም በኋላ በዊንዶስ ኦፍ አፍሪካ ልዩ-ፕሮጀክት ክልል (በጎልፍ ክለብ፣ በከተማ ደረጃ መናፈሻና በተለያዩ የህዝብ መዝናኛ) ህዝባዊ አገልግሎት የተያዘን የመንግስት ይዞታ፤ መሬት ባንክ የገባ መሆኑን እያወቁ የወንጀል ድርጊት መፈጸማቸውን ዐቃቤ ሕግ በክስ ዝርዝሩ ላይ ጠቅሷል።

ተከሳሾቹ የመሬት አስተዳደር የተለያዩ መመሪያና መተዳደሪያ ደንቦችን በመተላለፍ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ሊፈጠርላቸው የማይገባቸውን ዮርዳኖስ ዘውዲቱ እና ጓደኞቻቸው ሲሚንቶ አከፋፋይ ሕብረት ሽርክና ማህበር በሚል 2 ሺህ 905 ካሬ ሜትር ይዞታን የቦታ አጠቃቀም አነስተኛ ጥግግት ቅይጥ አገልግሎት በሚል ቦታው የተፈቀደበት አገልግሎት ድርጅት በማለት ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንዲሰጣቸው ማድረጋቸው በክሱ ዝርዝር ላይ ቀርቧል።

በዚህም ድርጊት በመንግስት ላይ ወቅታዊ የሊዝ ጨረታ ዋጋ 168 ሚሊየን 724 ሺህ 405 ብር ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸው ተመላክቷል፡፡

ከ16ኛ እስከ 19ኛ ተራ ቁጥር የተገለፁት ተከሳሾች ማግኘት የማይገባቸውን ጥቅም እንዲያገኙ ያደረጉ መሆናቸው ተጠቅሶ ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡

በተጨማሪም በህገወጥ መንገድ 17ኛ፣ 18ኛ እና 19ኛ ተከሳሾች በተለያየ ጊዜ 7 ሚሊየን 200 ሺህ ብር የእጅ መንሻ ሙስና የተሰጣቸው መሆኑን በክሱ ተመላክቷል።

ከ7 ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ ምንጩ እንዳይታወቅ እንዲሁም ወንጀል ፈፃሚው ከህግ ተጠያቂነት እንዲያመልጥ ለማድረግ ገንዘቡን በባንክ ሂሳባቸው በተለያየ መጠን ለሌሎች ቀሪ ተከሳሾች ያስተላለፉ እና የተጠቀሙ መሆናቸው ተጠቅሶ በዋና ወንጀል አድራጊነት በወንጀል የተገኘ ንብረት ወይም ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ተከሰዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ክስ ከቀረበባቸው ተከሳሾች መካከል ለ13ቱ ክስ እንዲደርሳቸው ያደረገ ሲሆን ክሱ የደረሳቸው የክስ መቃወሚያ ካላቸው ለመጠባበቅ እና ያልቀረቡት ለመጠባበቅ ለመጋቢት 15 ቀን 2018 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.