ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከዓለም አቀፉ የቴሌኮሙኒኬሽን ሕብረት ዳይሬክተር ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከዓለም አቀፉ የቴሌኮሙኒኬሽን ሕብረት ዳይሬክተር ኮስማስ ዛቫዛቫ (ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሕበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መረጃ÷ ኮስማስ ዛቫዛቫ (ዶ/ር) ጋር በዲጂታል ልማት ያለንን ትብብር ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ፍሬያማ ውይይት አድርገናል ብለዋል።
በውይይታቸውም ሀገራችን ቴሌኮምን ጨምሮ በዲጂታል መሠረተ ልማት ተደራሽነት፣ በዲጂታል ክህሎትና በተቋም ግንባታ እንዲሁም በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ትግበራ የተገኙ ተጨባጭ ውጤቶች አስደናቂ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ገልጸውልኛል ነው ያሉት።
የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ይበልጥ ለማፋጠን ከሕብረቱ ጋር ያለውን ትብብር ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር የዛሬው ውይይት ላቅ ያለ አበርክቶ እንዳለው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን የመሪነት ሚና ማሳደግና የሰው ሰራሽ አስተውሎት ለዲጂታላይዜሽንና ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን አጀንዳችን ያለው ፋይዳ በተመለከተም ምክክር አድርገናል ብለዋል።
የአቅም ግንባታ እና አዳዲስ የትብብር ዕድሎችን ማስፋት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይም መምከታቸውን አመልክተዋል።
በቀጣይም የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን ከግብ ለማድረስ እና ትብብራችንን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር በጀመርናቸው እና በሌሎች አዳዲስ ዘርፎች ዙሪያ በጋራ ለመስራት ተስማምተናል ነው ያሉት።
በዘርፉ የሚደረጉ ዓለም ዓቀፍ ኮንፈረንሶችን በኢትዮጵያ በማዘጋጀት ሀገራችን ይበልጥ ስራዋን ለዓለም እንድትገልጥ በጋራ ለመስራት እንዲሁም ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ እንዲሳካ ለመደገፍና በዘርፉ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንደሚቀጥል ከስምምነት ላይ ደርሰናል ሲሉም አብራርተዋል።