በኦሮሚያ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው አለ የክልሉ ሲቪል ሰርቪስና ሰው ሃብት ልማት ቢሮ።
የክልሉ የኮሙኒኬሽን ቢሮ ከክልሉ ሲቪል ሰርቪስና ሰው ሃብት ልማት ቢሮ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የውይይት መድረክ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ተደራሽ ማድረግ፣ በቴክኖሎጂና በሰለጠነ የሰው ኃይል ማደራጀት እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል።
የክልሉ ሲቪል ሰርቪስና ሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ኮከቤ ዲዳ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በክልሉ አምስት ከተሞች ተግባራዊ መደረጉን አንስተው÷ በዚህም የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተቻለ መሆኑን ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ በሁሉም አካባቢዎች አገልግሎቱን ተደራሽ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸው÷ ሕብረተሰቡ የሚያነሳባቸው የልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ማስቻል የሚለው ጉዳይ ትኩረት የሚፈልግ መሆኑን አመልክተዋል።
የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በተመለከተ ከ7 ሺህ 800 በላይ የተገልጋዮች ሐሳብ የሰበሰበው የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ በበኩሉ÷ የተገልጋዩን እርካታ ለማረጋገጥ ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን ገልጿል።
የአገልግሎት ፍትሐዊነት፣ የተገልጋይ ምልልስ መቀነስ፣ አካል ጉዳተኞችን ያማከለ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚሰራ ተገልጿል።
እንዲሁም አገልግሎት አሰጣጡን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ከማድረግ አንፃር በተገልጋዩ ዘንድ ቅሬታ እንደሚነሳ አንስቷል።
ከተገልጋዮች የተነሳውን ሐሳብ መነሻ በማድረግ ምላሽ የሰጡት የቢሮ ኃላፊዋ ኮከቤ ዲዳ÷ ማዕከላቱን ተደራሽና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ማድረግ እንዲሁም ከደላላ ነፃ የሆነ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማስቻል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
በተለይም ተገልጋዩ ቅሬታ የሚያነሳባቸው ጉዳዮች ምላሽ እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
አሁን ላይ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ብዙ ችግሮችን ለመፍታት እያስቻለ እንደሆነና በተለይም ተቋማት በመቀናጀት መስራት እንደሚጠበቅባቸው በመድረኩ ተነስቷል።
በሚልኪያስ አዱኛ