በመዲናዋ የትራንስፖርት ታሪፍ ላይ ማሻሻያ ተደረገ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ በወቅታዊ የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ የተደረገውን የዋጋ ማስተካከያ ተከትሎ የትራንስፖርት ታሪፍ ላይ ማሻሻያ አደረገ፡፡
አዲሱ የታሪፍ ማሻሻያ ከነገ መጋቢት 7 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን፥ ጭማሪው የከተማ አውቶቡስ አገልግሎትን ጨምሮ በሚኒባስ፣ በሚዲባስና የባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎችን ያካተተ ነው።
በመሆኑም የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ሁሉም ተቋማት፣ ባለንብረቶች፣ ማህበራትና ግለሰቦች በአገልጋይነት ስሜት ሕብረተሰቡን እንዲያገለግሉ ቢሮው ጠይቋል።
አገልግሎቱን በተገቢው መንገድ የማይሰጡና ሕብረተሰቡን ለተለያዩ እንግልቶችና ከተቀመጠው ህጋዊ ታሪፍ ውጪ የሚያስከፍሉ አገልግሎት ሰጪዎች ሲያጋጥሙ ሕብረተሰቡ ጥቆማ እንዲሰጥ ተጠይቋል።
በዚህም በነፃ የስልክ መስመር 9417 ወይም በአካል በአቅራቢያዎ በሚገኝ የትራንስፖርት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችና የትራንስፖርት ዘርፍ ባለሙያዎች የተሽከርካሪውን ሰሌዳና ሰዓት በመያዝ ጥቆማ መስጠት እንደሚቻል የተቋሙ መረጃ አመልክቷል።