Fana: At a Speed of Life!

ፍቼ ጫምባላላ ይቅርታ፣ መቻቻልና አብሮነት የሚጎለብትበት በዓል ነው – አቶ ደስታ ሌዳሞ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፍቼ ጫምባላላ በሰዎች መካከል ይቅርታ፣ መቻቻልና አብሮነት የሚጎለብትበት የፍቅርና መተሳሰብ በዓል ነው አሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ።

የሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ “ፍቼ ጫምባላላ” በዓል በዛሬው ዕለት በሀዋሳ ከተማ በተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች እየተከበረ ነው።

ሲዳማ የራሱ የሆነ ጊዜን፣ ወቅትንና ዘመንን የሚቀምርበት ባሕላዊ ዕውቀትና ጥበብ ያለው ሕዝብ በመሆኑ ይህን ባሕላዊ ዕውቀትና ጥበብ ከትውልድ ወደ ትውልድ እያሸጋገረ ለዚህ ትውልድ አድርሷል ብለዋል።

ጫምባላላ የተጣላ የሚታረቅበት፣ ቂም የያዘ ቂሙን የሚረሳበት፣ በሰዎች መካከል ይቅርታ፣ መቻቻልና አብሮነት የሚጎለብትበት እንዲሁም ፍቅርና መተሳሰብ የሚሰፍንበት ባህላዊ እሴት እንደሆነም ተናግረዋል።

የሲዳማ አባቶች ሕዝቡን ወክለው እንደሚጾሙ ገልጸው÷ እርቁ ከሰው ጋር ብቻ ሳይሆን ከአምላክ ጋርም የሚደረግበት ድንቅ ሥርዓት መሆኑን አስረድተዋል።

ፍቼ ጫምባላላ ለልጆች፣ ለእንስሳትና ለእንጨት ክብር የሚሰጥበት በዓል መሆኑን ገልጸው÷ ይህም የሲዳማ ሕዝብ ሰላም ፈላጊ ብቻ ሳይሆን ሰላምን የሚተገብር እንደሆነ ያሳያል ነው ያሉት።

በደብሪቱ በዛብህ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.