መንግሥት ሁሉንም የሃይማኖት ተቋማት በእኩልነትና በፍትሃዊነት ያገለግላል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ መንግሥት ሁሉንም የሃይማኖት ተቋማት በእኩልነት እንደ ዕሴቶቻቸውና አስተምህሯቸው በፍትሃዊነት ያገለግላል አሉ፡፡
ከንቲባ አዳነች ከኢትዮጵያ ወንጌላውያን፣ ካቶሊክ እና ከሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተክርስቲያናት መሪዎች ጋር “የሃይማኖት ተቋማት በመደመር መንግሥት እይታ” በሚል መሪ ሐሳብ ውይይት አድርገዋል፡፡
ከንቲባዋ ውይይቱን አስመልክቶ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት፣ የካቶሊክ እና የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተክርስቲያን በሰላም፣ ልማትና ትውልድ ግንባታ ሂደት ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማበርከታቸውን ገልጸዋል።
በዚህም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እንዲዳብር፣ ትውልድ እንዲማር፣ በስነምግባር እንዲታነፅ፣ ታሪክንና ቅርስን በመጠበቅ ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና አበርክተዋል ብለዋል።
ቴክኖሎጂን ወደ ሀገር በማስገባትና የሥራ ባሕልን በማበረታታት ረገድ ከሌሎች የሃይማኖት ተቋማት ጋር በመሆን ወሳኝ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ያሉት ከንቲባዋ÷ በታሪክ ብቻ ሳይሆን ባለፉት የለውጥ ዓመታትም ተቋማቱ በከተማችን ሁለንተናዊ የሰላም ግንባታ፣ የልማት እና የብልጽግና ጉዞ ላይ እያበረከቱት ያለው ተሳትፎ ጉልህ ነው ብለዋል።
በመድረኩ ለሕዝቦች ትስስር መጎልበት፣ በማኅበራዊ ልማትና በበጎ ፈቃድ ሥራዎች ተሳትፎ፣ የሥራ ባሕልን በማስረጽ፣ ትውልድን በሥነ ምግባር በመገንባት፣ የበጎነት ስራ መስራት እንዲለመድ በማድረግ፣ ለመልካም አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ መጎልበት፣ ሰላምን በማስፈንና ሕገወጥነትን በመከላከል ረገድ ለኢትዮጵያ ብልጽግና እና ለብሔራዊ ጥቅም በጋራ ለመቆም መወያየታቸውን አስረድተዋል፡፡
ውይይቱ በስራ ሂደት ያጋጠሙ አንዳንድ ክፍተቶችን እና እንግልቶችን በቀጣይ በትብብር ለማረም የሚያስችል ምቹ መደላድል መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡
መድረኩ በየክፍለ ከተማ ሲካሄዱ የቆዩ ውይይቶች ማጠቃለያ መሆኑን ገልጸው÷ የመንግሥትንና የሃይማኖት ተቋማትን ሚና እና ድርሻ በግልጽ ለይቶ ያስቀመጠ ነው ብለዋል።
የወንጌላውያን፣ የካቶሊክ እና የኢትዮጵያ የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተክርስቲያን መሪዎች ላደረጉት ከፍተኛ ተሳትፎ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ከንቲባዋ ባለፉት ሁለት ቀናት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሃይማኖት አባቶችና አመራሮች እንዲሁም ከእስልምና እምነት አባቶች እና ምዕመናን ጋር መወያየታቸው ይታወሳል።