Fana: At a Speed of Life!

በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ላይ ያተኮረው የአፍሪካ ቀዳማዊት አመቤቶች ፎረም በመዲናዋ…

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በድህነት ቅነሳና በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ላይ ያተኮረ የአፍሪካ ቀዳማዊት አመቤቶች ፎረም በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

መድረኩ የበካይ ጋዝ ልቀት መጠንን በመቀነስ የተጀመሩ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ሥራዎችን ለማጠናከር ያለመ ሲሆን÷ የተለያዩ አፍሪካ ሀገራት ቀዳማዊት እመቤቶች እና ተቋማት አመራሮች በገጽ ለገጽና በበይነ መረብ እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ፎረሙ በአፍሪካ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማትን ይበልጥ በማስፋፋት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና ድህነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ መፍትሄዎችን ለማመላከት እንደሚረዳ ተገልጿል።

በመድረኩ የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ረገድ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ ያስመዘገበችውን አመርቂ ውጤት በተሞክሮነት ታቀርባለች።

በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ከዛሬ ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት በሚካሄደው ፎረም የአፍሪካ ቀዳማዊት አመቤቶች በድህነት ቅነሳ እና በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ላይ ይመክራሉ።

የፎረሙ አስተባባሪና የአካሺያ ትሬዲንግ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታከለ ማሞ እንዳሉት፥ መድረኩ የቴክኖሎጂ ልውውጥና በሌሎች ዘርፎች ያለውን ትስስር ለማጠናከር ጉልህ ሚና አለው።

በኢትዮጵያ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን በሚገባ ለማስተዋወቅ እንደሚያስችልም አብራርተዋል።

ተሳታፊዎች በመዲናዋ ቆይታቸው የተከናወኑ የኮሪደርና ሌሎች የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው እንደሚጎበኙ ተናግረዋል።

መድረኩን አካሺያ ትሬዲንግ፣ የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን እና ሌሎች ተቋማት በትብብር አዘጋጅተውታል።

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.