ከንቲባ አዳነች የዒድ አል ፈጥር በዓልን አስመልክቶ ከ100 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ማዕድ አጋሩ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የዒድ አል ፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ ከ100 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ማዕድ አጋርተዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች÷ ድጋፉ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ አቅመ ደካሞች፣ አካል ጉዳተኞች እንዲሁም ጧሪና ደጋፊ ለሌላቸው የመዲናዋ ነዋሪዎች የሚደረግ ነው ብለዋል፡፡
ይህ የማዕድ ማጋራት መርሐ ግብር በሁሉም የከተማዋ ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች እየተካሄደ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡
በዚህ የረመዳን ወቅትም 27 ሺህ ያህል ወገኖቻችን ወሩን በሙሉ በ28ቱም የምገባ ማዕከሎቻችን የኢፍጣር ፕሮግራም ተዘጋጅቶላቸው ያለ ችግር እንዲያሳልፉ አድርገናልም ነው ያሉት።
የማዕድ ማጋራት የምናደርገው ጊዜያዊ ችግርን ለመቅረፍ ብቻ ሳይሆን ለሕዝባችን ያለንን ክብር ለመግለጽ እንዲሁም ወንድማማችነትን እና የእርስ በርስ መደጋገፍ እሴትን ለማጎልበት ነው ሲሉ አውስተዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች በማዕድ ማጋራት ሥራዎች ላይ በማስተባበር፣ አቅመ ደካሞችን በጉልበታቸው በማገዝ ደፋ ቀና ለሚሉ ወጣቶችና ካላቸው ቆርሰው ለመስጠት ለማይሳሱ ባለሃብቶች ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ለዛሬው ማዕድ ማጋራት ድጋፍ ያደረጉትን የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አሕመድ እና የዩናይትድ ዓረብ ኤምሬትስ ኤምባሲንም በልዩ ሁኔታ አመስግነዋል፡፡